Archive | May 1, 2018

“እኛም አገር ያለን ዜግነታችንም ኢትዮጵያዊ መስሎን ነበር! ከእርሻ ማሳችን ባዶ እጃችን ቀረን፤ ያለካሳ ከቤት ንብረታችን ልንፈናቀል ነው”

 

አንድ ሰው በአንድ አገር ወይም ክልል ወይም አከባቢ ሲወለድ ወዶና ፈቅዶ በራሱ ምርጫ የሚያድረገው አይደለም። ነገር ግን ሲወለድ ያገኘው ሲያድግ የተለማመደውና የተቀበለው የራሱ አገር ይሆናል። ወላጆቹም ቢሆኑ ድሃ ሆኑ ሀብታም ያለምንም ማንገራገር የሚቀበለውና ራሱን አሳምኖ ለነገ ኑሮ ራሱን የምያዘጋጅበት እንጂ ይህ የኔ አገር አይደለም ምርጫዬም አይደለም አልቀበለውም ብል ከአምዕምሮ ወጭ ሆኖ እንደምናገር ሰው እንጂ ተቀባይነት የለውም። እኛ በጋሞ ጎፋ ዞን ስንካለል፥ የጎፋ ብሔረሰብ ሆነን ስንኖር እንዲሁም በየቀበሌያችንና አከባቢያችን ስንወለድ መርጠን የተቀበልነው ሳይሆን የፈጣሪ ምርጫና ፈቃድ እንደሆነ ሁሉም የምገነዘበው ይመስለናል።

አሁን በየዕለት ኑሮአችን ጥላ ያጠላብን፥ መኖርን ያስመረረን፥ ግራ ያጋባን፥ መሄጃ ያሳጣን፥ መፍትሔ የነፈገን፥ አገራችን ኢትዮጵያ የእኛ እንዳልሆነች የምያሳየን በአከባቢው የመንግስት መዋቅር፥ በዞን መንግስት መዋቅርና በክልል የመንግስት መዋቅር የተቀመጡና አንዳንድ ከእነርሱ የጥቅም ተጋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተወካዮች ናቸው።

አገራችን ኢትዮጵያ የእኛም ከሆነች፥ እኛም ኢትዮጵያዊ ከሆንን ቀጥሎ ለማን አቤት እንደምንል ግራ ብገባንም ጉዳዩ የሚመለከተውና ሀላፊነት ያለው አካል መብታችንን እንዲያስከብርልን፥ ለጥያቄያችን መልስ እንድሰጠን፥ በደላችንን እንዲያይልን እኛ በደቡብ ክልል፥ በጋሞ ጋፋ ዞን፥ የደምባ ጎፋ ወረዳ የጉራዴ ቀበሌ አርሶ አደሮች ፍትሐዊና ትክክለኛ አስተዳደራዊ ምላሽ እንድሰጠን እንጠይቃለን፤ የአቤቱታ ጩኸታችንን እናሰማለን።

ከኦቶሎ ሳውላ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ (ፋል የሚባል) በመንገድ ሥራው ምክንያት በእርሻችን ላይ ጎርፍ ለቆብን ከእርሻ መሬታችን ነጻ ወጥተናል። ጎርፉ ደለል፥ አሸዋና ጠጠር ስለቆለለብን እርሻችንን ማረስ አንችልም፥ ከጥቅም ውጭ ሆነናል። በተደጋጋሚ ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄ አቅርበናል ሰሚ አጣን፥ ለዞን አስተዳደር በደብዳቤና በአካል ቀርበን ጠይቀናል፤ እንዲሁም ለደቡብ ክልል ቅሬታ ሰሚ አካል በደብዳቤና በአካል ቀርበን አቤት ብለናል። ላለፉት አምስት አመታት መፍትሔ ፍለጋ የተለያዩ በሮችን አንኳኩተናል፥ በትራንስፖርትና በአልጋ ኪሳችንን አራቁተናል፥ ድካምና እንግልት ደርሶብናል፥ ከአመራር አካላት ስድብና ዘለፋ ተፈራርቆብናል። ለረጅም ዓመታት ስናርስበት፥ ስንገለገልበት፥ ስንገብርበት፥ ልጆቻችንን ስናስተምርበት፥ ቤተሰቦቻችንን ስንመግብበት ለአገር ልማትና ዕድገት የደርሻችን ስንወጣ የኖርንበት መሬት ያለ ተገቢ ካሳና ተለዋጭ መሬት ሳይሰጠን መንገድ ተቀይሶበታል የጎርፍ መቀልበሻ ተቀዶበታል፤ ከእርሻ ማሳችን ነፃ ወጥተን ከነቤተሰቦቻችን ሜዳ ላይ ወድቀናል። ሰሚ ካለን የአስተዳደር ያለ! የፍትህ ያለህ! የሰሚ ያለህ! የፍርድ ያለህ! እንላለን።
ይህ ሳያንስ ሌላ ጫና፥ ሌላ በደል፥ ሌላ ማፈናቀል፥ ሌላ የፍትህ መንፈግ እየተፈፀመብን ነው። ይኽውም የጉራዴ ቀበሌ ነዋሪዎች ሳይስማሙበት፥ ካለፊቃዳቸው ውጭ ከዚህ በፊት በደንባ ጎፋ ወረዳ ሥር ሲተዳደር የነብረን ቀበሌ ወደ ከተማ መዋቅር በራሳቸው ፈቃድ በማን አለብኝነት ማዛወራቸው ነው። ያለ ህዝብ መስማማት፥ ያለበቂ ውይይትና ምክክር ከእንግዲህ ወዲህ የጉራዴ ማህበረሰብ የምተዳደረው በሳውላ ከተማ አስተዳደር መዋቅር ሥር ነው በማለት ባለቤት እንደለሌው ንብረት ገበያ ላይ አውጥተው አንዱ መዋቅር ለሌላኛው ሽያጭ አካሂደውብናል። ትናንትና የፈፀሙብን በደል ሳያንስ ከጋሞ ጎፋ ዞን ጋር በመመሳጠር ለአትክልቶቻችንና በእርሻችን ላፈራነው እህል ተገቢ ካሳና ግምት ሳይከፍሉ መሬታችንን ለመቀማት ፈልገው የሚያድረጉት ሤራ ስለሆነ የሚመለከተው አካል ቶሎ እንዲደርስልን እንጠይቃለን። ህይ ድርጊታቸው የሰው ሕይወት መጥፋትን፥ የንብረት ውድመትን፥ በአከባቢው የሰላም ውድመትን ሳይስከትል ተገቢ ምልሽ እንድሰጠን እናመለክታለን።
አንዳንድ የአስተዳደር አካላትና ጥቅም ፈላጊዎች ውስጥ ለውስጥ በህዝብ መካከል አለመተማመንን እየዘሩ በመንግስት ላይ ጥርጣረ እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱልን እንጠይቃለን። መብታችንን በጠየቅን ቁጥር ፀረ ሰላም ሀይሎች መባላችን ይቁም፥ ተገቢ ምልሽ ይሰጠን።
አርሶ አደሮች