Archives

20ኛውን የዓለም ዋንጫ ምን ልዩ ያደርገዋል?

world cop 2

ደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ ይፋጠጡበታል፤ 9.6 ቢሊዮን ዶላር  የሚያወጡ ተጨዋቾች ይሳተፉበታል፤ ከ5 በላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አራቅቀውታል፤  በኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ተሟሙቋል
20ኛው ዓለም ዋንጫ ባለፈው ሐሙስ ብራዚል እና ክሮሽያ በሳኦ ፓውሎ በሚገኘው ኮረንቲያስ ስታድዬም ባደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ 30 ደቂቃ የፈጀው የዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ስነስርዓት በ7.6 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተዘጋጅቷል፡፡ ትናንት ምሽት ሜክሲኮና ካሜሮን ሲገናኙ፤ ሌሎቹ  ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የ19ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ስፔን እና ሆላንድ የተገናኙበትና ቺሊ ከአውስትራሊያ የተጋጠሙባቸው ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መታየት ያለባቸውን ለመጠቆም ያህል፤ ዛሬ  እንግሊዝ ከጣሊያን፤ ነገ አይቬሪኮስት ከጃፓን፤ ሰኞ ጋና ከአሜሪካ፤ ማክሰኞ  ጀርመን ከፖርቱጋል፤ ረቡዕ ብራዚል ከሜክሲኮ፤ ሐሙስ ኡራጋይ ከእንግሊዝ ይገናኛሉ፡፡

በቴክኖሎጂ ድጋፍ ዳኞች ይራቀቃሉ፤  ማህበረሰብ ድረገፆች በመረጃ ያሟሙቃሉ
20ኛው ዓለም ዋንጫ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ በመራቀቅ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ለውጥ እየታየበት ነው፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ለስፖርት አፍቃሪው በርካታ መረጃዎችን በማቅረብ በአስደናቂ ሁኔታ ተሟሙቋል፡፡
የመጫወቻዋ ኳስ “ብራዙካ” ባላት የቴክኖሎጂ ጥራት የምንግዜም ምርጥ የዓለም ዋንጫ ኳስ ተብላለች። “ብራዙካ”ኳስ ያቀረበው ከእግር ኳስን ጋር በአጋርነት በመስራት ከ60 ዓመት በላይ የቆየው የጀርመኑ አዲዳስ ነው፡፡ አዲዳስ ለዓለም ዋንጫ አዲስ የኳስ ምርት ሲያቀርብ የዘንድሮዋ “ብራዙካ” 12ኛዋ ናት፡፡
በብራዙኳ ኳስ አመራረት ላይ ከተጨዋቾች ሊዮኔል ሜሲና ሴባስትያን ሸዋንስታይገር፤ ከክለቦች የአውሮፓዎቹ ባየርሙኒክና ኤሲሚላን እንዲሁም የብራዚሎቹ ክለቦች ፖልሚራስና ፍልሎሚንሴ በተግባር ሙከራዎች ተሳትፈዋል፡፡ በአጠቃላይ የብራዙካን ብቃት አስተማማኝ ለማድረግ አዲዳስ 287 የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾችን አስተያየት በመጠየቅ ሰርቷታል፡፡ በፓኪስታን ሲየልኮት በተባለች ስፍራ በሚገኘው የፎርዋርድ ስፖርት ፋብሪካ ተመርታለች፡፡
በሌላ በኩል  በአዲዳስ እና ናይኪ ኩባንያዎች ለተጨዋቾች የቀረቡ ታኬታዎች ለኳስ ቁጥጥር እና ምት የሚመቹ ሆነው ተዘጋጅተዋል፡፡ ከሞቃታማው የብራዚል አየር የሚታደጉ እና በልዩ ቴክኖሎጂ ሰውነት የማቀዝቀዝ ብቃት ያላቸው ማልያዎችና ሙሉ የስፖርት ትጥቆችም ቀርበዋል፡፡ ከሁሉም ግን የውድድር ዳኞች በተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በመታገዝ በአስተማማኝ ሁኔታ ግጥሚያዎችን እንዲመሩ በማስቻል ዓለም ዋንጫውን ልዩ ገፅታ አላብሰዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ አፈፃፀምም የሚያጓጓ ነው፡፡ የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው በ12 ስታድዬሞች በሚገኙ 24 የግብ መረቦች ላይ ይገጠማል። በእያንዳንዱ መረብ ላይ 7 ካሜራዎች የሚገጠሙ ሲሆን እነዚህ ካሜራዎች በሰከንድ አምስት መቶ ምስሎችን በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመቱ ኳሶችን ተከታትለው ይቀርፃሉ፡፡ የመሃል ዳኞች አንዳንዴ ለውሳኔ የሚቸገሩበትን ሁኔታ ለማስቀረት፤ የግብ መስመር ያለፉ ወይም ያላለፉ ኳሶችን ለማፅደቅ እና ለመሻር ፤ የሰው ልጅ አይኖች በሰከንድ 19 ምስሎች መመልከታቸውን በማሻሻል የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገለፃል፡፡ ወደ ጎል የተመታች ኳስ የግብ መስመሩን ስታልፍ የመሃል ዳኛው ያሰረው ሰዓት ላይ ከንዝረት ጋር ጎል የሚለው መልክት ይበራለታል፡፡ የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂውን የሰራው የጀርመን ኩባንያ ጎልኮንትሮል የመሳርያዎቹን ብቃት ለመለካት በብራዚል ብቻ 2400 ሙከራዎች ያለአንዳች ስህተት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በዓለም ዋንጫው 33 የመሃል ዳኞች ጨዋታዎችን የሚመሩ ሲሆን በእያንዳንዱ 40 ሰከንድ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ የስራ ጫና አለባቸው፡፡
የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው ይህን የዳኞች ከባድ ሃላፊነት በማገዝ እንደሚጠቅም ተጠብቋል፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአንድ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ የሚሸፍነው ከ7 እስከ 12 ማይሎች ርቀት ከምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋች 7 ማይሎች ርቀት ይልቃል፡፡ ምርጥ ዳኞች ከፍተኛው ፍጥነታቸው 20.7 ማይል በሰዓት ሲሆን የልብ ምታቸው በደቂቃ እስከ 160 ምቶች ነው፡፡ የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ በአንድ የዓለም ዋንጫ ስታድዬም ለመግጠም 260ሺ ዶላር የሚጠይቅ ሲሆን በአንድ ጨዋታ ተግባራቱን ለማከናወን 3800 ዶላር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የተነሳም ቴክኖሎጂው ከዓለም ዋንጫ ውድድር ውጭ ተግባራዊ ለማድረግ ይከብዳል፡፡
ሌላውም የዓለም ዋንጫው ቴክኖሎጂ ለዳኞች ስራ መቀላጠፍ የተሰራ ነው፡፡ ቅጣት ምትን የሚመታበት ቦታ ምልክት የሚደረግበትና ግድግዳ በመስራት ለመከላከል የሚቆሙ ተጨዋቾችን ለመገደብ የሚሰመርበት “ቫኒሺንግ ስፕሬይ” ነው፡፡ ከተሰመረበት በኋላ በንኖ ለመጥፋት ከ45 እስከ 2 ደቂቃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በአርጀንቲናዊ ጋዜጠኛ የተፈለሰፈ ሲሆን በመላው ዓለም ተሞክሯል፡፡
ዓለም ዋንጫው በታዋቂዎቹ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ዩቲውብ፤ ኢንስታግራም እና ሌሎችም ላይ በሚኖረው ሽፋን ዲጂታል ዓለም ዋንጫ ሆኗልም እየተባለ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ሰሞን 8.8 ቢሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በሚያደርጉት የመረጃ ክትትል የሚፈጠረው መጨናነቅ በሪከርድ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ ከዓለም ህዝብ 90 በመቶው ዓለም ዋንጫውን በማህበረሰብ ድረገፆች እየተከታተለ ሲሆን በ203 አገራት የስርጭት  ሽፋን ያላቸው የማህበረሰብ ድረገፆኙ በዓለም ዋንጫው ደንበኞቻቸውን ለማብዛት የተለያዩ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ፕሮግራሞችን በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
የማህበረሰብ ድረገፆቹ በዓለም ዋንጫው በቲቪ ከሚሰሯቸው ማስታወቂያዎች በተሻለ ስኬታማ መሆናቸውንም እየገለፁ ናቸው፡፡ የትዊተር ሃላፊዎች እንደገለፁት ገና ዓለም ዋንጫው ሳይጀመር ስለውድድሩ በሰፈሩ መልዕክቶች ከ4 ዓመት ደቡብ አፍሪካ ካስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ የላቀ ተከታታይ አፍርተዋል፡፡ፊፋ ለ23ኛው ዓለም ዋንጫ የከፈተው ኦፊሴላዊው የፌስቡክ ድረገፅ እስካሁን ከ20 ሚሊዮን በላይ ወዳጆች ያፈራ ሲሆን  ኦፊሴላዊ የትዊተር ድረገፁ ደግሞ  እስከ 5 ሚሊዮን ተከታዮች አፍርቷል፡፡ የማህበረሰብ ድረገፆችን ከሚጠቀሙ 1.2 ቢሊዮን የዓለም ህዝቦች 40 በመቶው ያህሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡

ስለ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ የተሰጠ መግለጫ

The Amharic Version
ስለ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ
የተሰጠ መግለጫ

Teddy4

ባለፉት ወራቶች ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም “ቴዲ አፍሮ” ከኮካ ኮላ እና በስፋት ሲወራ ከከረመው የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ያለንን አቋም እንድንገልፅ በሚጎርፍልን ጥያቄዎች ምክኒያት ከፍተኛ ጫና ስደረግብን ቆይተናል፡፡ በበኩላችን በተገባው የውል ስምምነት ላይ የግንኙነቱን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን የገባን እና ማክበር የነበረብን ቢሆንም ቅሉ የቴዲ አፍሮ እና የኮካ ግንኙነት ወሬ እንዴት አፈትልኮ ወጥቶ ህዝብ እንዲያውቀው እንደቻለ ቢያስገርመንም አሁን ለመገንዘብ እንደቻልነው ቴዲ ከኮካ ጋር ያለውን ግንኙነት ኢትዮፒካ ሊንክ በተሰኘ የአገር ውስጥ የኤፍ ኤም ሬዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆች አማካኝነት ያወጀው እና በሚያስገርም ሁኔታ ለኮካ የቲቪ ሥራም አድናቆቱን በመስጠት ያረጋገጠው የኮካ ኮላ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብራንድ ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ምስክር ሙሉጌታ መሆኑን መረዳት ችለናል፡፡
ያለጥርጥር በኮካ ኮላ ስም ቴዲ አፍሮ ለኮካ የቴሌቪዥን ስራ በማገናኘት እና በዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተነሳሽነቱን የወሰደው የብራንዱ ሥራ አስኪያጅ ነበር፡፡ እኛም ጥያቄውን ውድ አገራችንን በመላው የአለም ዋንጫ ተመልካቾች ዘንድ አዎንታዊ ገፅታ የትኩረት እይታ ስር የሚያውላት በመሆኑ እና በዚህ በጉጉት በሚጠበቀው ታላቅ ዓለምአቀፍ የስፖርት ክንዋኔ ግዙፍ ቁጥር ያለው የዓለም ህዝብ ዘንድ የአገራችንን እና የህዝባችንን መልካም ገፆች ለማሳየት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለምናደርገው ጥረት ሲባል በፍፁም ቅን ልቦና ተቀብለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሚለቀቅበት ወቅት የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ የቴዲ አፍሮን ዓለም አቀፍ እውቅና እና ዝና፣ የሥነ ጥበብ ገፅታ እና ስብዕና የበለጠ ከፍ እንደሚያደርገው እና እንደሚያጠናክረው በሚገባ እንገነዘባለን፡፡
ለታፈረችው አገራችን፣በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ለሚገኙት ለውድ አድናቂዎቻችንና ለሰው ልጆች ሁሉ ባለን የማይታጠፍ ታማኝነት በኮካ ፕሮጄክት ተሳታፊ መሆናችን ትክክለኛ እና አግባብነት የነበረው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም ምክኒያት የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ የቴሌቪዥን ቀረፃው የተሻለ ውጤታማነት ይኖረው ዘንድ ቴዲ አፍሮ በበኩሉ አቅሙ የቻለውን ያህል ጊዜውን፣ጉልበቱን እና ስነ ጥበባዊ ክህሎቱን በመጠቀም አስፈላጊውን ጥረት አድርጓል፡፡ በኮካ ሰቱዲዮ ፕሮጄክት ተሳታፊ የመሆኑ ዋነኛው ፋይዳ አለም አቀፍ ተዋቂነት ባለው ብራንድ በመጠቀም የኢትዮጵያን አዎንታዊ ገፅታ ለማጉላት የመላውን ዓለም ህዝብ ትኩረት ለመሳብ የሚያስችል ከባድ ያለ ተልዕኮ ለመወጣት እንጂ የንግድ ዕቃ በማስተዋወቅ ለሚያስገኘው እምብዛም ያልሆነ ጥቅም አልነበረም፡፡
በመሆኑም ሙዚቃ ነክ ንብረቶችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለኮካ ኮላ የማዕከላዊ ምስራቅ እና ምዕራብ አፍሪካ ለመስጠት ወኪል የሆነው ማንዳላ ቲቪ የዝግጅት ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ዴቪድ ሣንደር፣ በኮክ ስቱዲዮ የተሰራው የቴዲ አፍሮ ስራ በሚያስደንቅ እና በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን የሚገልፀውን ስሜት ቀስቃሽ እና አጓጊ ዜና እና ብስራት የተቀበልነው በከፍተኛ ክብር፣ ኩራት እና እርካታ ሲሆን ይህው ሰው ከዚያም አልፎ “የአለም ዋንጫ ቪዲዮው ተዘጋጅቶና ተከፋፍሎ ምናልባት በጥር ወር በኮካ ኮላ ይለቀቃል” በማለት አረጋግጦልናል፡፡ ከሥራው መጠናቀቅ በኋላ በውጤቱ የተደሰቱት የቴሌቪዢን አዘጋጆች እዚያው ላይ ቴዲ አፍሮ በአንድ የኮካ የሙዚቃ አልበም ተሳታፊ ይሆን ዘንድ ያቀረቡለትን ጥያቄ ወዲያውኑ በመቀበል በሥራው የተሳተፈ ሲሆን ይህም ስራ “የአዲስ አመት ክንውን” ሆኖ ባለፈው “ታህሳስ 22 ቀን በአራት አገሮች ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እንዲጫወት ተደርጓል፡፡”
ከበርካታ ቀናት በኋላ፣ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ መለቀቅ በጉጉት በምንጠባበቅበት ወቅት አቶ ምስክር የተጠናቀቀውን የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ እንድንመለከተው የጋበዘን ሲሆን በአርቲስቱ ሥራም እንደ ቴሌቪዢን አዘጋጆች ሁላችንም በጣም ደስተኛ ነበርን፡፡
ከጥቂት ጊዜ ባኃላ ግን ከባዶ መነሻነት አስደናቂ መጠማዘዝ ያሳየው አቶ ምስክር ፍርሐት በሞላው ድባብ በተጠናቀቀው ሥራ ላይ የነበረው የቴዲ አፍሮ ተሳትፎ እና ሽፋን “ዝናውን የሚመጥን አይደለም” በሚል የተጠናቀቀው ሙዚቃ እንዳይለቀቅ ድጋፍ እና ተቀባይነት ለማግኘት የሙከራ ጥረት አደረገ፡፡ ይህንን አቋሙን እንቀበልለት ዘንድ ለማሳመን ያደረጋቸው ሁሉም ጉዞዎች እና ኩነቶች በጉዳዩ ላይ “የቴሌኮንፈረንስ” እንዲካሄድ በመጠየቅ ከመታጀቡ በተጨማሪ በእርሱ አስተሳሰብ “ውድቀት” ሊሆን ስለሚችለውና የያዘውን አቋም አስመልክቶ ቴዲ አፍሮ ለህዝብ እንዳይገልፅበት እንድንታቀብ አስከማስፈራራት የደረሰ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ከመነሻው ጀምሮ በኮክ ፕሮጄክት ተሳታፊ እንዳልነበረ እና የኮካ ወኪል ከሆነው ከማንዳላ ቲቪ ጋር እንድንገናኝ ለማድረግ እና እኛን ለማሳመን እንዳልተሳተፈ ሁሉ አቶ ምስክር ከስራው ጋር በተያያዘ ከኮካ ኮላ ጋር የነበረን ግንኙነት በማስተባበል ራሱን በማራቅ ብሔራዊ እና ህዝባዊ ሃላፊነቶችን በተጋረደ ጠባብ የግል ጥቅም ለመለወጥ በፈፀመው አሳፋሪ፣ አገር ወዳድነት በሌለው የፈሪ ተግባሩ ኃላፊነትን ላለመሸከም በማሰብ ራሱን የማሸሽ እንቅስቃሴ አደርጓል፡፡
በኮካ ሰቱዲዮ የዝግጅት ሥራ አስኪያጅ በኩል ከቴክኒክ አኳያ የተጠናቀቀው ስራ የላቀ ጥራት እንዳለው በተደጋጋሚ ተረጋግጦልናል፡፡ በመሆኑም የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃን ይዞ በማቆየት እንዳይከፋፈል እና እንዳይለቀቅ የተደረገበት ምክኒያት እና የመጨረሻ ውሳኔ ከአርቲስቱ ወይም ከሥራ አስኪያጁ ጋር ምንም ውይይት ሳይደረግ እና ሳያውቁት በአቶ ምስክር ሙሉጌታ እና በኮካ ወኪል ማንዳላ ቲቪ የተሰጠ የጋራ ውሳኔ ነው፡፡
የተጠናቀቀው ሥራ ተሰራጭቶ እንዲለቀቅ በተደጋጋሚ የጠየቅን ቢሆንም፣ ከወኪሉ በመጨረሻ ላይ ያገኘነው ምላሽ ግን “በዚህ ደረጃ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅጂ ሙዚቃ ለጊዜው አንለቀውም” በሚል የተገለፀልን ከመሆኑ በላይ በእኛ ዘንድ የተፈጠረውን ሃያል ቁጣ በማባበል ለማቀዝቀዝ የሚሞክር እና ሥራውን ወደፊት ሊለቁት እንደሚችሉ ለማሳመን የሚጥር ማታለያ እና ለምንወዳት አገራችን፣ ለሁሉም ራሱን ለሚያከብር ኢትዮጵያዊ፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የአገር ውስጥ እና የውጪ አድናቂዎች እና ለአርቲስቱ በቁስል ላይ እንጨት የመስደድ ያህል ሆኖብናል፡፡
በበኩላችን በተጠናቀቀው ሥራ ላይ ስለተወሰደው ተገማችነት ላልነበረው የዱብዳ እርምጃ ለአቅረብነው ጥያቄ ማብራሪያ እና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው በርካታ ጥረት ትኩርት የተነፈገው ወይንም ከነጭራሹ ችላ ከመባሉ ውጪ ምላሽ የተሰጠውም ትዕግስታችን ከተሟጠጠ በኋላ ነበር፡፡
በመጨረሻም ምንም እንኳን በጉዳዩ ጭብጥ ዙሪያ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ስለተያዘው አቋም የተወሰነ መግባባት ላይ ለመድረስ ቴሌኮንፈረንስ የሚመለከታቸው ወገኖች እንደሚገኙበት ቃል ተግብቶበት የተዘጋጀ ቢሆንም ውይይቱ ሙያዊ በሆነ መልኩ ያልተዘጋጀ፣ ግልፅነት የጎደለው፣ አለመግባባት እንዳይከሰት ለማድረግ የጋራ መፍትሔ ለመሻት ሳይሆን ቅንነት በጎደለው መልኩ ይኛን ሐሳብ ለመረዳት ነበር፡፡ ቴሌኮንፈረንሱ ሆነ ተብሎ ህጋዊ ወኪል የሆነውን ሥራ አስኪያጃችንን በጭብጦቹ ላይ ለመወያየት እንዳይሳተፍ በማግለል መካሄዱ በራሱ ሂደቱ በቅን ልቦና ላይ ያለተመሰረተ መሆኑ ግልፅ ማስረጃ ነው፡፡
በመሆኑም የአርቲስቱ አድናቂ ለሆኑት ኢትዮጵያዊያን እና የውጪ አገር ዜጎች በሙሉ ከኮካ ኮላ ጋር የነበረንን ግንኙነት የቆረጥን መሆናችንን ለመግለፅ መገደዳችን እያዘንን ስንገልፅ የዓለም ዋንጫ እስከሚከፈትበት ዕለት ድረስ ኮካ ኮላ የወሰደውን እርምጃ በድጋሚ እንዲያጤነው ያደርግ ዘንድ በተደጋጋሚ ጥሪያችንን ስናቀርብ ብሔራዊ ጠርዝ ባለው እና በውድ አገራችን፣ በህዝባችን እና አድናቂዎቻችን ላይ ጭምር የተቃጣውን የፈሪ፣ እና አገር ወዳድነት የጎደለውን አሳፋሪ የክህደት እና ክብር የሚያጎደፈውን ተግባር ግን ይቅር ላለማለት ወስነናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አስከመጨረሻው ዕለት ድረስ ኮካ ኮላ የተጠናቀቀውን ሥራ እንዲያሰራጨው እና እንዲለቀው ግፊት ማድረጋችንን እንደምንቀጥልበት ለአድናቂዎቻችንን እያረጋገጥን ከዚሁ ጎን ለጎንም ከሁኔታዎች ጋር አግባብነት ያላቸውን ሰላማዊ እርምጃዎችንም በመውሰድ የሁለቱንም ወገኖች ገፅታን እና ጥቅምን የሚጎዳ ማናቸውም ውዝግብ በማስቀረት በአድናቂዎቻችን የተጣሉብንን አደራ መተማመን እና እምነትን ለመመለስ የሚያስችል እርምጃ የምንወስድ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡
ጉዞዉ ይቀጥላል!