Archives

ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ዘርፈው ጠፉ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

pile-of-one-hundred-dollar-bills

-ከተጠርጣሪዎቹ ሁለቱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ናቸው

የውጭ ገንዘቦችን መደበኛ ባልሆነ ግብይት ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ የሚዘረዝሩ ሰዎችን፣ አንድ መቶ ሺሕ ዶላር እንዳላቸው በመግለጽ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ላይ ዘርፈው ጠፍተዋል በሚል የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች፣ ድርጊቱን ከፈጸሙ ከግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በኋላ ባሉት አጭር ቀናት ውስጥ መያዛቸው ታወቀ፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሆኑት የአድማ በታኝ ተሽከርካሪ ሾፌሮች ኢንስፔክተር ዘለቀ አየለና ዋና ሳጅን ቀለብ ባዜ ሲባሉ፣ ሌሎቹ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ መሆናቸው የተገለጸው ተጠርጣሪዎች መሠረት ወዳጄ፣ ትዕዛዙ መለስ፣ ብርሃኑ ዳምጠውና ወንዴ ማኔ እንደሚባሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. መሆኑን፣ የድርጊቱ አፈጻጸም ምንጮች ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ አንድ ወጣት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ካሉ የውጭ ገንዘብ መንዛሪዎች ዘንድ በመሄድ የተለያዩ ገንዘቦችን እየመነዘረ ወዳጅነት ይመሠርታል፡፡

ወጣቱ ሌሎች ደንበኞችንም እየላከላቸው ከመንዛሪዎቹ ጋር ወዳጅነቱን በማጥበቁ ምክንያት በፈጠረው ቀረቤታ፣ በተጠቀሰው ዕለት አንድ ግለሰብ የአንድ መቶ ሺሕ ዶላር ምንዛሪ እንደሚፈልግ ይነግራቸዋል፡፡

በደህና ቀን ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩት መንዛሪዎቹ ከጓደኞቻቸውና ከራሳቸው በማሳሰብ 2.2 ሚሊዮን ብር በኰንትራት ላዳ ታክሲ ይዘው ወደ ሲኤምሲ ማምራታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ቡና ንግድ ድርጅትን፣ ዲሚትሪ መጋረጃ ሥራንና ጃክሮስን ሲያልፉ መጀመሪያ ወደ መንዛሪዎቹ የመጣው ወጣት ስልክ በመደወል ከሌላ ሰው ጋር ከተነጋገረ በኋላ፣ ትንሽ እንደሄዱ አንድ በእጁ ጥቁር ቦርሳ የያዘ ሰው ዘንድ ሲደርሱ ያቆሙለትና ወጣቱ ወርዶ እሱ ይገባል፡፡

ጥርጣሬ የገባቸው መንዛሪዎች፣ ‹‹የያዝከው ገንዘብ የታለ? እኛ የምንሰጥህንስ ገንዘብ በምን ትይዘዋለህ?›› በማለት እየጠየቁት ሲጓዙ፣ ከፊት ለፊታቸው አንድ የፌዴራል ፖሊስ ተሽከርካሪ ድንገት መጥቶ ይቆምና የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት የፌዴራል ፖሊስ አባላትና አራት ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች በመውረድ ላዳ ታክሲው ላይ መሣሪያ ይደግኑበታል፡፡

በላዳው ተሳፍረው የነበሩትን በሙሉ በማጉላላትና በሰደፍ በመምታት ወደ ፌዴራል ፖሊስ ተሽከርካሪ በማስገባት ‹‹በሕገወጥ ድርጊት ተጠርጥራችኋል›› ብለው ታክሲውን ‹‹ተከተለን›› በማለት መንገድ ሲጀምሩ፣ የታክሲው አሽከርካሪ ወደኋላ በመመለስ ማምለጡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

መንገድ ላይ የተሳፈረውና ጥቁር ቦርሳ ይዞ ነበር የተባለው ግለሰብ፣ ‹‹እኔ የመጣሁት ከእስራኤል ነው፡፡ አሁንም ለሕክምና ልመለስ ነው፡፡ ይኼንን ቦርሳ ውሰዱትና እኔን ተውኝ፤›› ሲላቸው መንገድ ላይ አውርደውት 2.2 ሚሊዮን ብር የያዙትን መንዛሪዎች ይዘዋቸው መሄዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ገንዘባቸውን ያስረከቡዋቸውን መንዛሪዎች ወደ አንድ ጫካ ውስጥ በመውሰድ በሆዳቸው እንዲተኙ ካደረጉ በኋላ፣ ተጠርጣሪዎቹ በያዙት ተሽከርካሪ ወደኋላ በመመለስ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ በሚባለው አካባቢ ገንዘቡን ተከፋፍለው ለጥቂት ቀናት ተሰውረው መክረማቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ 2.2 ሚሊዮን ብር የተዘረፉት ግለሰቦች ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጋቸው፣ ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል በጥቂት ቀናት ውስጥ ሁሉም በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

Source : ethiopianreporter

አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለማግኘት ያሰቡ ግለሰቦች ሁለት ሚሊዮን ብር መዘረፋቸው ተጠቆመ

 ተጻፈ

በአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በሕገወጥ መንገድ የውጭ አገር ገንዘቦችን የሚዘረዝሩ ግለሰቦች፣ አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለማግኘት የማያውቋቸው ግለሰቦች ዘንድ ሄደው ሁለት ሚሊዮን ብር መዘረፋቸው ተጠቆመ፡፡

 pile-of-one-hundred-dollar-bills

በዕለተ ሰንበት እሑድ ግንቦት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የስልክ ጥሪ የደረሳቸው ግለሰቦች ስለሚያገኙት ሥራና ትርፍ እንጂ ሊገጥማቸው ስለሚችለው ችግር አለማሰባቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በደረሳቸው የስልክ ጥሪ ‹‹አንድ መቶ ሺሕ ዶላር አለን›› ያሏቸው ግለሰቦችን ማንነት ሳይሆን፣ የሚገኙበትን ሥፍራ ብቻ መጠየቃቸውን አውስተዋል፡፡

በእጃቸው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ቀርቶ ምንም ነገር ያልያዙት ግለሰቦች ያሉበትን ቦታና የያዙትን የተሽከርካሪ ዓይነት ሲነግሯቸው፣ ተዘራፊዎቹ ግለሰቦች ሁለት ሚሊዮን ብር ይዘው ለመድረስ ጊዜ እንዳልፈጀባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸክመው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለመግዛት የሄዱት ግለሰቦች የጠበቃቸው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ሳይሆን መሣሪያና ከፍተኛ ማስፈራሪያ በመሆኑ፣ ምንም ሳያንገራግሩ ሁለት ሚሊዮን ብራቸውን እንዳስረከቡ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

የደረሰባቸውን ተጨማሪ በደል መግለጽ ያልፈለጉት ተዘራፊዎች፣ የተንቀሳቀሱበት ጉዳይ ሕገወጥ ቢሆንም ገንዘቡ ሁለት ሚሊዮን ብር በመሆኑ ያዋጣናል ወዳሉትና የመጀመሪያው የሕግ ማስከበሪያ ቦታ ወደሆነው ፖሊስ ማምራታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሆኑትን ሁሉ ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡት ተዘራፊዎቹ፣ የዘራፊዎቹን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲገልጹ በፖሊስ ሲጠየቁ፣ መሣሪያ የያዙና ፈርጣማ አቋም ያላቸው መሆናቸውን  በዝርዝር ማስረዳታቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡

ጉዳዩን ይዞ ሁለት ሚሊዮን ብር ዘርፈው የጠፉትን ግለሰቦች እያፈላለገ ነው የተባለውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር