Archives

እየተላቀሱ ሲሸኛኙ መኖር! (ነፃነት ዘለቀ)

ነፃነት ዘለቀ

ትናንት ማታ ባለቤቴ ዐይኗ ድልህ መስሎ ከጎረቤት ስትመጣና እኔ ሥራ ውዬ በዚያውም የምንገኝበት ወቅት፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ያጀበው የኹዳዴ ፆም ከመሆኑ አንጻር አልፎ አልፎ እንደማደርገው “የማታ ትምህርቴን” በስሱ ተሣትፌ ቤቴ ስገባ አንድ ሆን፡፡ በልቅሶ ስትነፋረቅ እንዳመሸች ከጉንጮቿ መርጠብና ከዐይነ ውኃዋ ያስታውቃል፡፡ ስሜቷ ልክ አልነበረም፡፡

ምን እንደሆነች ጠየቅኋት፡፡ የሆነውን ሁሉ አስረዳችኝ፡፡ ባለቤቴ ስታለቅስ ያመሸችው በጉርብትናም፣ በቡና ተርቲበኛነትም፣ በጓደኝነትም ትቀራረባት የነበረችው አንዲት ሴት ወደ ዐረብ ሀገር ለግርድና ሥራ ለመሄድ ድንገት ስትነሣ በዚያ ደንግጣና በወጣትነት የዕድሜ ክልል የምትገኘው ይህች ሴት ትዳሯንም፣ ለእህል እንጂ ለሥራ ያልደረሱ ሕጻናት ልጆቿንና ባለቤቷንም፣ ማኅበራዊ ሕይወቷንም… ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጋ ወደ ማታውቀው የስደት ዓለም ልትነጉድ መዘጋጀቷን ተመልክታ ከልቧ በማዘን ነው፡፡ እኔም ካንጀቴ አዘንኩ፡፡ ነገር ግን ዕንባ የለኝም፡፡ በኅሊናም በአካላዊ ዐይንም ላለፉት 25 እና ከዚያ በላይ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሳለቅስ በመቆየቴ አሁን አሁን ሌላው ቀርቶ እኔ ራሴ እንኳን ብሞትና ፈጣሪ ለራሴው እንዳለቅስ በማይመረመር ጥበቡ ለአፍታ ዕድሉን ቢሰጠኝ አንዲት ዘለላ ዕንባ የሚወጣኝ አይመስለኝም፡፡ ዕንባችንንም ጨረስነው፡፡ በውነቱ ብዙ ሰው ዕንባውን ጨርሷል፡፡ “እዬዬም ሲደላ ነው” መባሉም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የምታለቅሰው እኮ የሀዘንና የርህራሄ ስሜት በሰውነትህ ሲበዛ ነው፡፡ አሁን ዘመኑ የቋሚ ሀዘንና የቋሚ ልቅሶ በመሆኑ ይመስኛል ብዙዎቻችን ሁሉንም ሀዘንና መርዶ ከመላመዳችን የተነሣ አዲስነቱም ብርቅነቱም እየቀረ ጥቂት የማንባል ሰዎች ወደተንቀሳቃሽ ሜካኒካዊ ፍጡርነት ተለውጠናል፡፡

ዕድሜ ለተከታታይ መንግሥቶቻችን ችግርን እንደጉድ ተላመድነው፤ እሥርን በጣም ተላመድነው፤ ስደትንም ተላመድነው፤ ስቃይንም ተላመድነው፤ ግርፋትንም ተላመድነው፤ በሽታንና ርሀብንም ተላመድነው፤ ግፍንና በደልን ተላመድነው፤ ኢፍትሃዊነትን ገንዘባችን አደረግነው፤ ሙስናን ጌታችን አደረግነው፤ ገንዘብን/ንዋይን  የፈጣሪያችንን ቦታ አስረክበነው እንደጣዖት አመለክነው፡፡ ምን ቀረን? ምንም፡፡ በነዚህና ሌሎች ተያያዥ ክፍለ ዘመናዊ መጥፎ ክስተቶች የተነሣ አንዳችን ለአንዳችን አንተዛዘን አልን፡፡ እጅግ መጨካከንና እርስ በርስ መበላላት ዓለምን ወርረዋት ልናይ የመገደዳችንን ምሥጢር ጊዜ የሚፈታው መሆኑ እንዳለ ሆኖ አሁን ግን ማኅበረሰባችንን ስንታዘብ በሁሉም ረገድ የወረደ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለማንኛውም ባለበቴ ግን ስትነፋረቅ እንዳመሸች እንዳትዘነጉባት – ለየት ባለ መልክ እሷ ሆደ ብቡ ናት፡፡

ልጂቱ የምትሄደው ወደ አንዱ ዐረብ ሀገር ነው፡፡ ትዳር አላት፡፡ ልጅም አላት፡፡ ቤት እየተከራየች ልትነገድ ሞከረች፡፡ ግን አልተሣካላትም፡፡ ኪራዩ ሰማይ ነው፡፡ በዚያ ላይ እንደአካሄድ ልነግድ ብለህ ከመጀመርህ ቀበሌዎች ይመጡብሃል፡፡ መጥተው በአነስተኛና ጥቃቅን የሚሏቸው የራሳቸው ድርጅቶች በአባልነት እንድትታቀፍ ይጠይቁሃል – ጅብ ይቀፋቸውና፡፡ በአንድ ለአምስትና ለአሥር ተደራጅተህ በነሱ ቁጥጥር ካልገባህ ደግሞ ያጠፉሃል፡፡ ወደለማኝነት ወይም እንደዚህች ልጅ ስደትን እንድትመርጥ ይገፉሃል፡፡ ምንም ዓይነት ሌላ ምርጫ አይሰጡህም፡፡ ራስህን ማጥፋት ከፈለግህም ሙከራህ እስከተሳካ ድረስ በህግ የማያስጠይቅህ አንደኛው መጥፎ አማራጭ ነው፡፡ ግራ የሚያጋባ ዘመን ነው፤ ጉቦው ደግሞ አይቻልም፡፡ በእግርህ ሄደህ የሚፈጸምልህ አንድም ነገር የለም፡፡ ካለ ጉቦ የመቀበሪያ ቦታና የፍትሀት ጸሎት ማግኘት ራሱ የማይቻልበት የለዬለት የጥፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በገንዘብ አንቀባርረህ የማትይዛቸው የነፍስ አባት ከሌሉህ – ለምሳሌ – ጸሎቱ የተካለበና በቶሎ አፈር ለማልበስ ሁሉም የሚቸኩልበት የቀብር ሁኔታ ነው የሚፈጠረው – አይበልብህና አስቀያሚ ዕድል ገጥሞህ ብትሞት ማለት ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ለስደት እየተዳረጉ ነው፡፡ ያላገባና ያልወለደ ሰው ቢሰደድ ዕዳው እንደገብስም ባይሆን ቀለል ይላል – ግለሰባዊ መጥፎነቱ እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን የወረደብን መቅሰፍት ገደብ ያጣ ነውና ሕጻናት ልጆችን ጥለው፣ የሞቀ ትዳር ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ቸልሰው፣ የደረጀ ማኅበራዊ ትስስርን በትነው… ለአደገኛው የስደት ኑሮ የሚጋለጡ ወገኖቻችን በእጅጉ ያሳዝናሉ፡፡ ሀገራቸውን መልካም ሰው ቢያስተዳድር ኖሮ ለዚህ ባልተጋለጡ ነበር፡፡ ሰው አጣን፤ እኛም ሰው መሆን አቃተን፡፡ ከላይ ያለው ከኛው የሄደ ስለሆነ እኛ ላይ የተሟጠጠ ስብዕና እላይ ሊያቆጠቁጥ አይችልምና ከቤታችን ጀምረን እኛው ሰው ብንሆን ደግ ነበር፤ እስኪ ሰው እንፍጠር፡፡ ልጆቻችንን በአግባብ እንኮትኩት፡፡ ችግሩ ከላይ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በዋናነት ከሥር ከቤተሰብ ነው፡፡ መለስ እኮ ከሰማይ አልወረደም – ከቤተሰብ ነው፣ ከተበለሻሸ ቤተሰብ፡፡ መንግሥቱ እኮ ከምድር አልፈለቀም – ከቤተሰብ ነው – በቅጡ ካልተገነባ ቤተሰብ፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከኛው ነውና ራሳችንን እንፈትሽ፡፡…

የተዛባ ወይም የፈረሰ ትዳር እንዴት ይቃናል? የወላጅን ፍቅር አጥቶ የሚያድግ ልጅ የተወለጋገደ ሥነ ልቦናው እንዴት ይስተካከላል? ስደት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሰዎች በሀገራቸው ሰርቀው ካልሆነ በትክክል ሠርተው መኖር ስለማይችሉ ቀዳሚ ምርጫቸውን ስደት አድርገዋል – በበኩሌ አልፈርድባቸውም፡፡ “በሀገርህ ሠርተህ ያልፍልሃል” የሚሉ ወገኖች ደግሞ ያስቁኛል፡፡ አለማፈራቸውም ያስገርመኛል፡፡ የክርቶስን አባባል በመጠኑ አንሻፍፌ ልጠቀምበትና እውነት እውነት እላችኋለሁ – (በአሁኑ ወቅት በተለይ) ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርታችሁ ከሚያልፍላችሁ ይልቅ ዝኆንና ዓሣ-ነባሪ በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልኩ ይቀላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ቅያስ በምንኖር ሰዎች በኔ መንደር ውስጥ ለምሳሌ ልጅ ወይ ሚስት ወይ ባል ወይ እህትና ወንድም በአብዛኛው ወደዐረብና ሌሎች ሀገራት በስደት ያልሄዱበት፣ ያ ባይሆን በዚያ Diversity Visa (DV) በሚሉት ሀገር የሚያስክድ ሰይጣናዊ አንደርብ ወደአሜሪካ ያላቀኑበት ቤት ማግኘት ይከብዳል – ቆዩኝማ ልቁጠርላችሁና እውነቱን ልንገራችሁ … አዎ፣ በኛ ጠባቧ ደሴት ውስጥ አሥራ አራት ያህል አባውራዎች አለን፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከውጪ አነሰም አደገም ገንዘብ የማይላክላቸው ሦስት ብቻ ናቸው – በኔ ዕውቀት ነው ታዲያ፡፡ እኔ ራሴ ቀደም ሲል ይላክልኝ ነበር – ሲያቀብጠኝ ግን “ለራሴ መሆን አያቅተኝም፤ ከኔ የባሰባቸውን ዘመዶቻችንን ደግፉ” ብዬ በመናገሬ የሆድ ምቀኛው አፍ ነው እንዲሉ ተቋረጠብኝ፤ አይቆጨኝም፡፡ ለሌላ ባልተርፍ ቢያንስ የቤተሰቤን ጉሮሮ በተገኘው ነገር እደፍናለሁ፡፡ ዕድሜ ለመንግሥቶቼ የኔ ቢጤ ሠራተኛ በማሊና በናይጄሪያ የራሱ ቤትና መኪና ሲኖረው እኔ ደግሞ ባቅሜ እግዜር የሰጠኝ 11 ቁጥር አለኝ – እግሮቼን ማለቴ ነው፤ ነገር እንዳታጣምሙና ከወንድሞቼ ጋር እንዳታጣሉኝ አደራችሁን፡፡

የሚገርማችሁና ወያኔም ሊኮራበት የሚገባው ነገር እኔ ባለሁለት ዲግሪው “ምሁር” ተብዬ ዜጋ ከ30 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ትናንት ከወለድኳት የራሴው ልጅ ከሆነች አንዲት የዐረብ ሀገር ገረድ ድጎማ የሚደረግልኝ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የታሪክ ምፀት መቼ እንደሚያልፍና ታሪክ እንደሚሆን አላውቅም – ባለንበት መርገጡንና የኋሊት መሮጡን ተፀይፈን አንድ ቀን ወደ አቶ ጊዜ ተገቢ መስመር እንደምንገባ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ያኔ ከቆሞቀርነት ነፃ እንወጣና ሌሎች የደረሱበት ደረጃ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለኝ – “ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ሦስት ሺህ ምናምን ዓመታት ገደማ ጀምሮ የቆመ የጊዜ ባቡር እስካሁንም እንደተገተረ ነው – እርሱ ሲሮጥና ሌሎች ሲጠቀሙበት እኛ ግን እያላገጥንበት በቀደምት አባቶች ታሪክ ብቻ ተኮፍሰን እንኖራለን…” ሲሉ መስማቴን ለማመልከት ነው ስለጊዜ እንደጅብራ መገተር በሾርኒ የምጠቁመው፡፡ አሁንና ዛሬ ግን የዛሬ ሃምሳ ምናምን ዓመታት በፊት ለአባቶቼና አያቶቼ ከሩቅ ቦታ ውኃ በበርሚል እየገፋ  ያመጣ የነበረ የዐረብ ጀማላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንገት ሳያስበው በነዳጅ አልፎለት ከንፍጥ በማይተናነስ አንጎሉ የኔን ዘሮች እንደእንስሳ ሲነዳና በዐውሬያዊ ደመነፍሱ ሲያሰቃያቸው ሳይ አለመፈጠሬን መረጥሁ፡፡ ይህን የኛንና የነሱን ነገር ስታስቡት እኛ ፈጣሪን ምን ብንበድለው ይሆን እንዲህ በኋሊዮሽ ሩጫ የጠመደን በሚል መጨነቃችሁ አይቀርም – ደንዝዘንና የአፍዝ አደንግዝ ምትሃታዊ የዲያቢሎስ መተት ተዙሮብን እንጂ የአሁኑ የሀገራችን ሁኔታ ላያሳብደው የማይችል ኢትዮጵያዊ ሊኖር ባልተገባ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ “ገረድ” የምለው የቤት ሠራተኛ ማለቱን አጥቼው አይደለም – ማይማኑ የሀገር መሪዎች ከገረድም የገረድ ገረድ ስላደረጉን ያን ሆን ብዬ ለመግለጥ ነው፤ እነዚህ መሪ ነን የሚሉ “ሰዎች” ይህን ሁሉ እያወቁ፣ በድርጊቱም ሳይቀር በደላላነት እየተሳተፉ የስቃያችን ዋና ተዋንያን መሆናቸውን ደግሞ አንርሳ፡፡)

ልጂቱ ባለቤቴን ጨምሮ መላውን ጎረቤት አስለቀሰቻቸው፡፡ በብዙ ቦታ እንዲህ ነው፡፡ መላቀስ፡፡ እየተላቀሱም መሸኛኘት፡፡ ሞትም እንደዚሁ ነው፡፡ የሞተ ሰው ምን እንደሚያጋጥመው አይታወቅም፡፡ የተሰደደም እንዲሁ፡፡ ቤቱን አፍርሶ ሄዶ በፎቅ ይጣል ይሆናል፤ ለአራትና ለአምስት ይ(ት)ደፈር ይሆናል፤ እንደሰው ሳይቆጠር ይደበደብና በፊቱ ላይ ምራቅ ይተፋበት ይሆናል፤ በሰውነቱ ላይ የፈላ ውኃ ወይም አሲድ ይከለበስበት ይሆናል፡፡ ብዙ ነገር ይደርስበት ይሆናል፡፡ በዚህ ሁሉ መከራና ስቃዩ ግን ያ የሚኖርበት ሀገር ብቻም ሣይሆን የሀገሬ መንግሥት የሚለው ከሃዲው ወያኔ ሳይቀር ተበዳዩን እንደወንጀለኛ በመቁጠር የግፍ ግፍ ይፈጽሙበታል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ በነዚህ ነቀዞችና ብሎች ምክንያት ኢትዮጵያ ሀገሩ  አንዲት እንጀራ ስላሳጣችው ነው፡፡ ይህች የተፈጥሮ ሀብት መጋዘን ለልጆቿ የሚሆን አንዲት ዳቦ አጣች! ሌሎች ባዕዳን ሲዘማነኑባትና ጓዳ ጎድጓዳዋን እንደልባቸው ሲፈነጥዙበት ልጆቿ ግን የስደትና የዐውሬ ሲሳይ ሆኑ፡፡ አዎ፣ ቅጣት ነውና እስኪያልፍ ማልፋቱ ያለ ነው፡፡

ይህች ልጅ እዚህ የረባ ገቢ አልነበራትም፡፡ ከእጅ ወደ አፍም መሆን አቃታት፡፡ ስለዚህ ብሞትም ልሙት፣ ቢያልፍልኝም እሰዬው ብላ ሄደች፡፡ ደመወዟ ወደሀበሻ ገንዘብ ሲመዘነር በወር ስምንት ሺህ ብር ገደማ ነው፡፡ ይህ ብር እርግጥ ነው ብዙ ይመስላል – በተለይ ለአንዲት የቤት ሠራተኛ፡፡ በኢትዮጵያ ይህ ገንዘብ በትንሹ ለአራት የባለ ቢኤ ዲግሪ ሰዎች ወርኃዊ ደሞዝ ነው፡፡ ይህች ልጅ ለቤትና ለምግብ አታስብም፤ ለሣሙናና ምናልባትም ለልብስ አታስብም ይሆናል፡፡ የሚገጥሟት ሰዎች ጥሩዎች ከሆኑ ደግሞ የተሻለ ዕድል ሊገጥማትም ይችላል፡፡ እኛ ግን እንዲህ ያለ ነገር በህልም እንጂ በእውን አናገኘውም፡፡ የበይ ተመልካቾች ነን፡፡ ያልተማረ ሀገርን እያደናበረ ሲገዛ የተማረ በቤት ተቀምጦ ልጅ አሳዳጊ ሆኗል – በሚስቱ ገቢ እየኖረ፡፡

ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ይህን ስትሰማ “አንተ ነፁ፣ እኔም ለሁለት ዓመት ልሞክረው እንዴ?” አለችኝ፡፡ ተናግራ ሳትጨረስ ዶሴየን ማገላበጥ ገባሁ፡፡ ብዙም ሳልለፋ የሰማኒያችንን ወረቀት በቅርብ አገኘሁትና “ሰማሽ ማንጠግቢቲ፣ ይህን ወረቀት ቡጭቅጭቅ አድርጌ ነው የምጥልልሽ! ምን ጎደለሽና ነው ዐረብ ሀገር ልሂድ የምትይ? በስተርጅና ‹ቀላዋጭ‹ ልታደርጊኝ ነው? በየወሩ ለአስቤዛ ብቻ የምሰጥሽ 1000 ብር ለኛና ለአራት ልጆቻችን አልበቃሽ አለ? እ? ወይ ጥጋብ! ምን አማረኝ ብለሽኝ አሳጣሁሽ? ‹ሥጋ ካማረሽ እዚያ ታች ያለው ሉካንዳ ቤት አጠገብ ሄደሽ ትንሽ ቆም ብትይ ሰዎቹ ሲያወራርዱት ታይና አምሮቱ ይወጣልሻል፣ ዓሣ ወይም አትክልትና ፍራፍሬ ካማረሽ ደግሞ እዚህ አጠገባችን ወዳለ ሱፐርማርኬት ጎራ ብለሽ ባይንሽ ጎብኘት አድርገሽ ብትወጪ ሁለተኛ ውል አይልሽም…› አላልኩሽም?…” በማለት ተቆጣኋት፡፡ ምኞቷንና የጋለ ፍላጎቷንም ወዲያው በረድ አደረገችና “ኧረ እውነትህን ነው ነፁ፣ ያጓደልክብኝ ነገርስ የለም፡፡ እንዲያው መኪና መግዛት ብንችል ብዬ ነበር እንጂ…” ስትለኝ ብልጭ አለብኝና “መኪና? መኪናም ያምርሻል? አንዲት ቪትዝ ነው ጥምዝ የሚሏት ብጥሌ መኪና 300 ሺህ ብር እየተገዛች፣ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ 2500 ብር እየተገዛ፣ አንድ የቤት መጥረጊያ ባቅሙ 80 ብር እየተገዛ፣ በዓለም ገበያ ጥንቡን የጣለ ቤንዚን በሊትር 17 ብር እየተገዛ፣ ባለ12 ቮልት የመኪና ባትሪ ዛሬ አልፎለት 2500 ብር እየተገዛ (በቀ.ኃ. ሥላሴ ዘመን ይህ ገንዘብ በትንሹ 5 ያገለገሉ ኦፔልና ታኖስን የመሰሉ መኪኖችን ይገዛ እንደነበር ማስታወሱ ትዝታን መቀስቀስ ስለሚሆንብኝ ልተወው)፣ አንድ ኪሎ ስኳር 20 ብር እየተገዛ፣ አንድ ኪሎ ሥጋ በርካሽ ሥፍራዎች 280 ብር እየተገዛ፣ ተራ ባለፔዳል ብስክሌት 7 ሺህ ብር እየተገዛ (እውነቴን ነውና እባካችሁን በመገረም ሣቁ!)፣ አንድ መናኛ ምግብ ከአንድ መናኛ ሆቴል በ100 ብር ተገዝቶ እየተበላ፣ አንድ ቢራ 15 ብር ተገዝቶ እየተጠጣ፣ አንድ ጃምቦ ድራፍት በ16 ብር እየተሸጠ፣ አንድ ግራም ባለ18 ካራት ወርቅ ከሺህ ብር በላይ እየተሸመተ፣ አንድ ሸሚዝ ከ500 ብር በላይ እየተገዛ፣ አብዛኛው የቀድሞው ንዑስ ከበርቴ ለአቅመ-ክንዴ ቡቲክ ለመድረስና ውራጅ ልብስ እንኳን ገዝቶ ለመልበስ ዕቁብ መግባት እያስፈለገው፣  … ባለበት በዚህ ቀውጢ ሀገራዊ ሁኔታ እንዴት አንቺን መኪና ሊያምርሽ ቻለ?” ብዬ አፋጠጥኳት፡፡ ለሴት እንዲሁም ለወንድ ፊት መስጠት ሰላለመደብኝ እንጂ በውስጤ ግን በጥያቄዋ ሳላምን ቀርቼ እንዳልነበረ እዚህ ላይ በንስሃ መልክ ማውረድ እፈልጋለሁ፡፡ ጉደኛ ኢትዮጵያ በአዲስ መልክ እየተገነባችላችሁ ነው፤ እውነተኛ ልጆቿን ወደመቃብር እያወረደች እንግዴ ልጆቿን ግን ወደ አራት ኪሎና ወደሀብቱ መንደር የምታወጣ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያ እየተሠራች ስለሆነ ለዚህ ፍጻሜ የተጋችሁ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ሤረኞች ሁሉ እስከዚያው ደስ ይበላችሁ፡፡ ስለነገው ግን ከአንድዬ በቀር እንኳን እኔ ሰይጣንም አያውቅም፡፡

እንግዲህ ያቺን ሴት ይቅናት ነው የምል፡፡ እርግጥ ነው ለ2 ወይ ለ4 ዓመታት በብዙ መስዋዕትነት የምታጠራቅመው ገንዘብ ምን ሊሠራ እንደሚችል መገመት አይከብድም – ዛሬ ቆጠራው በሚሊዮንና በቢሊዮን ሆኗል፡፡ በመቶ ሺዎች ቢኖርህ ምናልባት እስኪያልቅ ድረስ ብብትህን ወትፈህ ትጠጣበት ወይ ትበላበት እንደሆነ እንጂ ዘዴኛ ካልሆንክ ብዙም አይፈይድልህም – ገንዘቡን ዜሮ አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የወረደው እሳት ቀላል አይደለም፡፡ የብሩ ዋጋ እጅግ በመጋሸቡ በፌስታል ሙሉ ብር የምትገዛው ነገር በጣም ጥቂት ነው – ያሳቅቅሃል፤ ባልና ሚስቶችማ የጊዜው ዋና የጠባቸው መነሻ ይሄው የአጋንንት ውላጅ የሆነው ገንዘብ መሆን አለበት፡፡ የኃይሌ አንድ ብር የመንጌን አሥር ብር ቢያህል የወያኔን ደግሞ በአማካይ 500 ብር ይሆናል – ልታስበው ትችላለሀ፡- በብር አንድ ሺህ ይሠራ የነበረ አንድ መኖሪያ ቤት በተመሳሳይ አሠራር አሁን በትንሹ 600 ሺህ ብር ከፈጀ ግሽበቱ ስንት ዕጥፍ ነው? ሒሳብ ካላወቅህ ሰው ጠይቅና ተረዳ፡፡ የደርግ ጊዜው የስሙኒ ለስላሳ መጠጥ አሁን ከአሥር ብር በላይ ነው፡፡… ታዲያ ሰው ሁሉ ጠጪ የሆነው ወዶ መሰለህ? ባለው ገንዘብ ብርጭቆ ውስጥ ከመደበቅ በስተቀር የተሻለ ቁም ነገር ሊሠራበት አልቻለም፡፡ ስለሆነም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት አዳሜ ጆሮውን ወትፎ እስከውድቅትና ከዚያም ባለፈ ያገኘውን መጠጥ ሲቆጋ ያድራል፡፡ ንጹሕ ጉበት ይዞ መሞት ዱሮ ቀረ ወንድሜ!

እንደሚባለው ከሆነ ባለሥልጣናትና የጦር አበጋዞች የራሳቸው የሆነ የብር ማምረቻ ማሽን አላቸው አሉ፡፡ በድብቅ እያመረቱ ገበያውን ስለሚያጥለቀልቁት እኔን መሰሉን የወር ደሞዝተኛ ጨምሮ ድሃ መኖር አልቻለም፡፡ ብዙው ሰው ለሁለትና ሦስት እየሆነ ገንዘብ አጋጭቶ ግማሽ ኪሎ ሙዝ በመግዛት በዳቦ ይቀምሳል – ያ እንግዲህ ምሣ ወይ ራት መሆኑ ነው፡፡ በርሀብ ምክንያት በሽታን መቋቋም እያቃተው ፈንግል እንደገባባቸው ጫጩቶች በየቦታው የሚረፈረፈው ሕዝብ ብዙ ሆኗል፡፡  ሞታችንን በቁማችን ጨርሰን አሁን አሁን ጣራችን ቀላል እየሆነ መምጣቱ በአንድ በኩል ደግ ነው፡፡ አልጋ ላይ ብንወድቅ ማን ያስታምማል? በዚያ ላይ ህክምናውም ለጉድ ነው፤ አስታማሚም ገና ከመተኛትህ ሞትህን ወይ መዳንህን ይመኝልሃል – ፍቅር ጠፋ እኮ ወገኖቼ፡፡ ለምርመራ ብቻ የምታወጣው ቤትህን ይነቅላል፡፡ ኅሊና ብሎ ነገር እንደሆነ ጠፍቷል፡፡ ሰው ገንዘብ እንጂ ወገን ጨርሶ አይታየውም፡፡ ብላ ተባላ ነው ዐዋጁ፡፡ ዱሮውንም ማተቡን የሚበጥስ ሰው እምብርት እንደማይኖረው የታወቀ ነው፡፡

አሁን መንግሥት ስለሌለን መንግሥት እሰኪኖረን ድረስ ለመንግሥት የሚሆን መልእክት ለጊዜው የለኝም፡፡ ለሀብታሞችና ለኢንቬስተሮች ግን አለኝ፡፡

ብዙ ሀብታሞች “Take care of the pennies, the dollars will take care of themselves.” በምትለዋ አባባል እንደሚስማሙ አውቃለሁ ወይም ቢያንስ እገምታለሁ፡፡ በተወሰነ ደረጃ ትክክል ናቸው ብዬም አምናለሁ – መቼም አለኝ ብለህ አላግባብ ስትዘራ አትውልም፤ እንዲያ ማድረግም የለብህም፡፡ በባህላችንም “ገንዘብ ወዳጇን ታከብራለች” ይባላል፡፡ አሁንም እንደሚባለው ገንዘብ ጥሩ አገልጋይ ሲሆን መጥፎ ጌታ መሆኑን በማስታወስ ወደ መልእክቴ ልለፍ፡፡(Money is good servant, but bad master. ሲሉ የሰማሁ ወይ ያነበብኩ መሰለኝ፡፡)

ሀብታሞችና ኢንቬስተሮች ሆይ! ገንዘባችሁ ሰው ይሁን – ትልቁ ገንዘብ ሰው ነው፤ ሰውን ማዕከል ያላደረገ ገንዘብም ሆነ ሌላ ነገር ከንቱ ነው፡፡ የገንዘባችሁ ምንጭ በመጠኑ የእናንተ “ታታሪነት”ና ወሳኝ አመራር ሊሆን ቢችልም በዋናነት ግን በሥራችሁ ቀጥራችሁ የምታሠሩት ወገናችሁ ነው፡፡ እሱን አክብሩት፤ ውደዱትም፡፡ ያ ሠራተኛ ባይኖር ብቻችሁን የትም አትደርሱም ነበር፡፡ ያን ሠራተኛ ስትወዱትና ስታፈቅሩት ታስቡለታላችሁ፡፡ እንደሰው ቁጠሩት እንጂ እንደመገልገያ መሣሪያ አትቁጠሩት፡፡ በፈጣሪም ዘንድ ያሳጣችኋል፤ ያስወቅሳችኋልም፡፡ እውነት ለመናገር ለውሻቸው የሚጨነቁትን ያህል፣ ለውሻቸው የሚበጅቱትን በጀት ያህል ለሠራተኛቸው የማይጨነቁና በቅጡ የማይከፍሉ ሀብታሞች ሞልተዋል፡፡ “ሰው ቢሄድ ሰው ይተካል” የሚባለው ፈሊጥ ለመሣሪያ እንጂ አንተን አንቀባርሮ ለሚያኖር ሰብኣዊ ፍጡር ሊሆን አይገባም፡፡ ሀብታሞች ሆይ! የማሰብ አቅማችሁን ተጠቀሙ፡፡ ዛሬውኑ ሰው ሁኑ፤ ሰው ለመሆን ደግሞ ከአሁኑ መሞከር እንጂ በግድ በእርጅና ዘመን የሚቋቋምን የበጎ አድራጎት ድርጅት መጠበቅ አይገባም፡፡ ቀጥራችሁ የምታሠሩት ሰው እንደናንተ መኖር ያምረዋል፤ እንደናንተ መልበስ፣ እንደናንተ ባማረ ቤት ውስጥ መኖር፣ እንደናንተ መብላትና መጠጣት፣ እንደናንተ ገንዘብ በባንክ ማኖር፣ እንደናንተ መዝናናት፣ እንደናንተ … መሆን ያሰኘዋል – እንናንተው ሰው ነውና፡፡ ታዲያ ለምን ከናንተ አሳንሳችሁ እንደተንቀሳቃሽ ንብረታችሁም ቆጥራችሁ ታዩታላችሁ? እንኳን እሱ የሚለፋ የሚደክመው እናንተስ በጥቂት ድካም ባፈራችሁት ሀብት እንደዴቪስ ቲቶ ሰማይን እስከመጎብኘት ትዝናኑ የለምን?

ሀብታሙ ሰው ቤቱንና አኗኗሩን ይመልከት፡፡ ከዚያም ወደ አንድ የበታች ሠራተኛው ቤት ድንገት ጎራ ይበልና ቤቱንና አኗኗሩን ይጎብኝ፡፡ ከራሱ ሕይወት ጋር ያወዳድር፤ ያነጻጽር፡፡ እርግጥ ነው ከነርሱ ጋር አንድ ይሁን አይባልም፤ አንድ ዓይነት እንዲሆንም አይጠበቅም፡፡ ግን ልዩነቱ የሰማይና የምድርን ያህል ቢሆን ወንጀል ነው፤ ነውርም ነው፤ ባንዱ ላብ ሌላው ተቀማጥሎ የሚኖርበት ሁኔታ መሻሻል አለበት፤ በአነስተኛ ደሞዝ የሚቀጠረው ሠራተኛ መፈጠሩን እስኪጠላ መሰቃየት የለበትም – ዳኛው ደግሞ ኅሊና ይሁን እንጂ “ከከፋው ይልቀቅ!” የሚለው የበሉበትን ወጪት የሚሰብር ዕብሪታዊ አነጋገር መሆን አይገባውም – ድሃ ቢከፋ ምን መድረሻ አለው? የዓለምን ሀብትና ጥሪት የተቆጣጠሩት እኮ ከዓለም ሕዝብ አንድ መቶኛ የማይሆኑት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ መንግሥታትም የቆሙት በነዚህና ለነዚሁ የቀ … ነው፡፡ (የቀን ጅቦች ልል ስል እግዜር በጥበቡ አወጣኝ!)፡፡ ሀብታሙ ገንዘቡን የት ልጣለው እያለ ሌትና ቀን አሼሼ ገዳሜ ሲልበት ወይም በገንዘብ ብዛት አንዱ ከአንዱ እየተወዳደረ በባንክ ሲያጉር ድሃው ሠራተኛ ታምሞ ለህመም ማስታገሻ የሚሆነውን አስፕሪን መግዣ ሊያጣ አይገባም – ይህ ነገር በብዙ ቦታዎች እውነት ነው – በአፋጣኝ ሊስተካከል የሚገባው መራር እውነት፡፡ ሁሉም ሰው ራቁቱን ተወለደ፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ወይም ግፋ ቢል በአንዲት እራፊ ጨርቅ ተጠቅልሎ ይሄዳል – ከዚያም ጥርኝ ዐፈር ይሆናል፤ የርሱ ታሪክ እስከዚያች ሰዓት ነው፡፡ የሚኖረውም ሃምሳና ስልሳ ግፋ ቢል መቶ ዓመት ነው፡፡ ለዚህች አጭር ዕድሜ ታዲያ ለምን እንጨካከናለን? የሀብታችንና የክብረታችን መሠረት የሆነው የበታች ሠራተኛችን በበሽታና በርሀብ እየተሰቃዬ ዐይተን እንዳላየን የሚያደርገን ምን ዓይነት ተፈጥሯዊ ልክፍት ይሆን? ስለዚህ ሰው እንሁን፡፡ ሁሉም የሚያልፍ መሆኑን እንመን፡፡ ለምሳሌ ከመቶ ዓመት በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል እንገምት፡፡ አሁን የምናየው ነገር ሁሉ በርግጠኝነት የለም፤ መልካም ነገርን መሥራት ግን መቼም የማይሞት የኅሊናና የነፍስ ስንቅ ነው፡፡ በቃ፡፡ እኔም በቃኝ፡፡ ሰሚ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡