Archives

የአቋም መግለጫ በጨዋታ፤ አዎ ሁሉም ነገር ከፖለቲካችን ጋር የተያያዘ ነው… እንወራርድ!

suicidal

Abe Tokichaw

ትላንት አዲሳባ ውስጥ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ራሱን በገዛ ክላሹ አጠፋ የሚል በፎቶግራፍ የተደገፈ ዜና አየን፤ ከእርሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በቪዲዮ ማሰረጃ የሰማነው አንድ ዜና እንዳስረዳን ደግሞ፤ አንዷ ኮረዳ አራት ኪሎ ይሁን ጊዮርጊስ ካለው የእግረኛ መሸጋግሪያ ድልድይ ላይ ራሴን ፈጥፍጬ እገድላለሁ ስትል ፖሊስ እና የአካባቢው ህዝብ በማግባባት እና ብበልሃት ይዘዋት ራሷን ከማጥፋት ድናለች የሚል ነበር። እንግዲህ እነዚህ እኛ በሩቁ ሆነን የሰማናቸው እና ያየናቸው ናቸው። በቅርብ ሆነው የሚታዘቡ ደግሞ ብዙ እየታዝቡ ይገኛሉ…

ይህንን ጉዳይ ባወጋንበት ወቅት ”…እና ታድያ ማንም መሮት ራሱን ያጠፋ እንደሆን ፀሀዩ መንግስታችን ለዚህ ተጠያቂ መሆን አለበት ወይ… ሁሉም ነገርስ ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት አግባብ ነው ወይ…” የሚሉ ልማታዊ አስተያይቶች በብዛት ጎርፈውልኛል… መለሱ ….አዎ ሁሉም ነገር ከፖለቲካው ጋር ይያያዛል በሀገራችን ለሚከሰቱ ሞቶችም ሆነ ምሬቶች በሙሉ ፀሀዩ መንግስታችን እና ፖለቲካችን ተጠያቂ ናቸው። የሚል ነው…! አይ… የሚል ካለ እንወራረድ እና ዳኛ አስቀምጠን እንሟገት !

በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም አሰራ ዘጠኝ ሁለት ሺህ ሁለት አመተ ምህረት፤ በእንግሊዝ የታተመው ዘ ጋርዲያን የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ በወቅቱ እንግሊዝ ላይ ራስን የማጥፋት ርምጃ እየጨመረ መምጣቱን ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አገዛዝ ጋር አዛምዶ ዘግቦት ነበር። ቀረብ እናድርገው ካልን ደግሞ በቅርቡ የካቲት ስድስት ሁለት ሺህ አስራ አራት ቢቢሲ በድረ ገፁ በ ኢንግላንድ እና ዌልስ እየጨመረ የመጣውን ትዳር መፍረስ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ጋር አያይዞ ዘግቦታል። የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ፖለቲካዊ ችግር እንደሆነ አያጠያይቀም።

እንግዲህ ነገሮችን ፖለቲካዊ ይዘት ማላበስ በእኛ አልተጀመረም ለማለት ያክል ይቺን ቆንጠር አድርጌ ከጠቀስኩ ወደ ራሳችን ጉዳዮች ላሳልጥ፤

በኢትዮጵያችን ሁሉም ችግር ከፖለቲካው ጋር የተያያዘ ነው ወይ …አዎ!

ሰዎች ራሳቸውን እንዳያጠፉ፣ አውሮፕላን እንዳይጠልፉ፣ ከሀገር እንዳይጠፉ እንኳን ሌላ ቀርቶ አመለ ክፉ እንዳይሆኑ መፍትሄው ያለው በገዢዎቻችን እና በፖለቲካቸው እጅ ነው። አንድ ሰው ቢያንስ ኑሮ ካልመረረው በስተቀር ራሱንም አያጠፋም፤ ካገርም አይጠፋም። ኑሮ እንዳይመረን ለማድርግ ደግሞ ከሰማይ ቀጥሎ በላያችን ላይ የተከደነብን መንግስት ወሳኙን ድርሻ ይይዛል በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች በሚተገብራችው ተግባራት እንድንማር እንጂ እንዳንማረር ማድረግ መቻል አለበት፤ ካልቻለ ለሚችሉ ማስረከብ ወይም እግዜር እንዲያስችለው መፀለይ ይኖርበታል።

በሀገሪቱ ውስጥ የአዕምሮ ህምመተኞች ቁጥርም ሆነ የሰካራሞች ቁጥር መጨመር እንደው “የቤት ጣጣ ነው” ብለን የምናልፈበት የየዋሁ ዘመን አልፏል። አሁን ሁሉም ችግር የመንግስት እና የፖሊሲ ጣጣ ነው። እነ ያላቻ ጋብቻ እና ጠለፋ ሳይቀሩ የፖለቲካችን ችግር መገለጫዎች ናቸው። መንግስት በህጎቹ እና በደንቦቹ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት አለበት። አለበለዛ… ሂድ ወደዛ… መባሉ አይቀርለትም!

መንግስት አለ የሚባለው የመኪና መንገድ (አሰፋለት) የእግረኛ መንገድ (ኮበል ሰቶን) እና የባቡር መንገድ (ሃዲድ) ሲዘረጋ ብቻ አይደለም። ለእያንዳንዳችን አመቺ የኑሮ መንገድም መዘርጋት አለበት፤ የመንግስትም ሆነ የፖለቲካችን ዋና ጉዳይ ሰው ነው። የሰዎች ደህንነት ባልተጠበቀበት ሁኔታ ፖለቲካው ጤነኛ ነው መንግስቱም ደህነኛ ነው ልንል አንችልም።

እኛ እያንዳንዳችን ጤና ከራቀን መጀመሪያ መታከም ያለበት መንግስታችን እና ፖለቲካው ነው!

አዎ ሁሉም ችግር ፖለቲካ ነው! (አራት ነጥብ አሉ ሰውየው!)

Posted By Alemayehu Tibebu