Archives

የኢህአዴግ ዕኩይ የምርጫ ስልት ጅማሮ

ደሳለኝ አዴላ

ጀርመን

ጠቅላይ ሚንስቴር ሐ/ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሰሞን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በጽ/ቤታቸው ከተገኙ በርካታ ጋዜጠኞች መካከል ለአምስቱ ብቻ የመጠየቅ እድል በሰጡበት መግለጫ

ስለአገልግሎት ሰጪ መ/ቤቶች ድክመት ተጠይቀው የሰጡት መልስ ለፅሁፌ መነሻ እንዲሆን መርጫለሁ፡፡

WoyaneBalanceJustice

#የስልክ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት መቆራረጥ እና ዕራሽ አለመኖር ለቀጣዩ ምርጫ ስጋት አይሆንም

ወይ?$ ለሚለው ጥያቄ ጠ/ሚንስቴሩ ሲመልሱ #አያሰጋንም$ ብለዋል፡፡ የምንሰራው ባለፈው ምርጫ ህዝቡ

አስተዳድሩኝ ብሎ ድምፁን ስለሰጠን እንጂ ለሚቀጥለው ምርጫ ብለን አይደለም፡፡ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህ

ጎዶሎ መልስ ከሳቸው የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በምርጫ ፉክክር ያሸነፈ ለማስተዳደር የሚጥር ፓርቲ

ስለተመረጠ ይሰራል፣ እንዲመረጥም ቀልብ ገዢና አሳማኝ ዕቅዶችን ለህዝብ ይፋ እያደረገ እራሱን ያጫርታል፡፡

አልያ የህዝብ ቁጣ በትር በኮሮጆ በኩል ይደርሰዋል፡፡

በርግጥ ወያኔ መራሹ መንግስት ከህዝብ ለሚመጣ ቁጣ ግድ የለውም፡፡ ቁጣው ቢመጣም

የሚያስታግሰው ከታጠቁት መሳሪያ ዋጋ እጅግ ያነሰ የሰውነት ክብር በሚሰማቸው ታመኞቹ በመሆኑ፡፡

ጠ/ሚንስቲር ሐ/ማሪያም ይህን የድርጅታቸውን ልምድ በሚገባ ስለሚረዱ በአናቱም ለሚቀጥለው ምርጫ ምን

እየተደገሰ እንደሆነ ስለሚያውቁ ስጋት አይገባኝም ሲሉ መልሰዋል፡፡ በነገራችን ላይ ሰውዬው የሟቹ ጠ/ሚኒስቴር

ኮፒ መሆናቸውን ለማሳየት ከነስሙ እንደሚኮርጅ ሰነፍ ተማሪ ሆነዋል፡፡ ጥረታቸው ሁሉ የሚያሳየው ይህንኑ

ነው፡፡ ከላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንኳ ብዙ ተመሳሰሎች ታገኛለቸሁ፡፡ በዋናነት ደግሞ

የድርጅታቸው ዋና አዕማድ የሆነውን ውሸት፡፡

ወያኔ የምርጫ ወቅት እየተቃረበም ይሁን አይሁን ህዝብን በተለያየ መንገድና ጊዜ ይዋሻል፡፡ የመብራት

መቆራረጥ እንደማይኖር ከተነገረን ከ200 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ችግሩ ሊፈታ አልቻለም፡፡ የውሃ ነገር ከአዲስ

አበባ ውጪ የተለመደ በመሆኑ እንደጥያቄ አይነሳም፡፡ በአዲስ አበባ ግን ጠያቂ አይሰለችም ሆኖ በየእለቱ ሮሮውን

ያሰማል፡፡ ወያኔም በውሸት ተስፋ ያረካዋል እንጂ ጠብታ አያድለውም፡፡ ጠ/ሚንስትሩ ግን የአዲስ አበባ ህዝብ 75

በመቶ ለ24 ሰዓታት ያልተቋረጠ የውሃ አገልግሎት ያገኛል ሲሉ አፋቸውን ሳያዳልጣቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን

በተለያዩ ድርጅቶች የተደረገ ጥናት የሚያሳየው የአዲስ አበባ ውሃ ስርጭት ከ55 በመቶ እንደማይበልጥ ነው፡፡

ለዚህም በልማት ስም እየተነሱ ወደ ከተማይቱ ጥግ የተገፉ ሰዎች እንደ ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ቢጫ ጄሪካን

ከእጃቸው አለመለየቱ ምስክር ነው፡፡ የስልክና የኢንተርኔት ጉዳይ ቢከፋ እንጂ አይሻልም፡፡ የኮምንኬሽንና

የቴክኖሎጂ ሚንስቴር በሚንስቴር ደረጃ ተቋቁሞ በዶ/ር ደብረጽዩን እንዲመራ ቢደረግም እስካሁን የአገልግሎት

ዘርፉን ከማስፋፋትና ከጥራት ይልቅ የስለላ መሳሪያዎችን እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ በማስገባት የፍርሀቱ ማስታገሻ

ማድረግን ነው የመረጠው፡፡

ወያኔ እያንዳንዱ ዜጋ ምን በልቶ እንዳደረ ለማወቅ የሚጓጓ ፈሪ ፓርቲ እንደመሆኑ ምርጫ በደረሰ ቁጥር

ተርበትባች እርምጃዎችን ሲወስድ ተመልክተነዋል፡፡

ተርበትባች ስል ጤናማ ፍርሀት ፈርቶ ያልሸነፍ ባይነት ቅቡል ዲሞክራሲያዊ እርምጃ ይወስዳል ማለት

አልዳዳም፡፡ የድርጅቱ ባህሪም ይህን አይወድም አይፈቅድምም፡፡

ወያኔ ተርበትባች ነው ማለቴ በፈሪ ዱላ በርካታ ሀገራዊ ጥፋት ይፈፅማል ለማለት ነው፡፡ ቀደም ባሉት

የምርጫ ዘመናት በፍርሀት ተነሳስቶ ይወሰዳቸው እርምጃዎች እጅግ አስከፊና ነገን የማይሉ ሀገራዊ ጥፋቶች

ስለመሆናቸው አራቱንም ያለፉ ሀገራዊ ምርጫዎች መለስ ብለን ብንቃኝ ሀሳቤን በሚገባ ያጠናክሩልኛል፡፡

በ1987 ዓ.ም. የመጀመሪያው ምርጫ ሲካሄድ የወያኔ #ስጋት የነበረው ኦነግና ደጋፊዎቹ$ ላይ እጅግ

የመረሩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ወያኔ በወቅቱ ኦሮሚያን የማጣት ፍርሀቱ ከፍተኛ ስለነበር ከኦነግ ደጋፊዎችና

አባላት አልፎ #ስለኔ ክፉ ስታወሩ ተሰምታች%Eል$ ያላቸውን የሀገር ሽማግሌዎች ሳይቀር ያለማስረጃ በአባዱላ

መሪነት አስገድሏል፡፡ ለዚህም በተለይ የአንቦና የወለጋ ነዋሪዎች ቋሚ ምስክሮች ነቸው፡፡ ሁለተኛው ምርጫ

በ1992 ሲካሄድ የነበረው እውነትም ዲሞክራሲያዊነት የነገሰበት እንደነበር ነው ታሪክ የሚመሰክረው፡፡

የጊዜው ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ብዙ መከራ ተቀብለዋል:: ተነጣጥለው

መወዳደራቸውም ዋጋ አስከፍሏቸው አልፏል፡፡

የ1997 ምርጫ ብዙ የተባለለት ስለሆነ ማሰልቸት እንዳይሆንብኝ እፈራለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ የዚህ ምርጫ

ሂደት የማይደገም መስሎ እና የወያኔን ፍርሀት ከእጥፍ በላይ አንሮ አልፏል፡፡ 97 የወደፊቷ ኢትዮጵያ የነፃነትና

ዲሞክራሲያዊነት ተስፋ አጨልሟል፡፡ በወጣቱም ላይ የማያባራ የበቀል በትሩን እስካሁን እንዳይታጠፍ

አድርጎታል፡፡ ከሁሉ በላይ ሟቹ ጠ/ሚንስትር የ97ቱ አይነት ምርጫ #መቼም የማይደገም$ እንደሆነ አስረግጠው

ነግረውን አልፈዋል፡፡

የ2002ቱ አራተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግብአተ መሬት አዋጅ የታወጀበት፣ የወያኔ

መሪዎችም አፋቸውን ሞልተው ለ40ና 50 አመታት ስልጣን ይለቃል ብላችሁ የምታስቡ እርማችሁን አውጡ

ያሉበትን ክስተት አስተናግደንበታል፡፡ በዚህ ምርጫ በወያኔና በካድሬዎቹ የተወሰዱ ኢዲሞክራሲያዊና ኢሰብዓዊ

ድርጊቶችን ማንም አይረሳቸውም፡፡ ዶ/ር መራራ ቅጥር ነብሰ ገዳይ አሰማርተው ፖሊስ አስገድለዋል የመባሉ

አስቂኝ ወሬ፣ ፕ/ር በየነ በመብራት ሀይል አዳራሽ በተናገሩት ቃል ምክንያት የደረሰባቸው የእናስርሀለን ዛቻ ከሁሉ

የከፋው ደግሞ በምርጫው ትልቅ ድል ይገጥመዋል የተባለለት አንድነት ፓርቲ መሪ የወ/ት ብርቱካን ዳግም እስር

ሳይጠቀሱ የማያልፉ ናቸው፡፡

የቀጣዩ ምርጫ ሂደትና ግብ በወያኔና ነተቀናቃኞቹ ነተቀናቃኞቹ ነተቀናቃኞቹ ሰፈር

ይህ አፋኝ ስርዓት ለመጪው ምርጫ እኩይ ስትረቴጂውን ከወዲሁ ጀምሮታል፡፡ በተቃራኒው

ተፎካካሪዎቹ በድብ ውስጥ ሰጥመው የቀሩ መስለዋል፡፡ ይህ ዓመት ለምርጫ የሚሆን መደላድል የሚሰናዳበት

የሰው ሀይልና የገንዘብ ምንጭ ስትራቴጂዎች በይፋ ለህዝብ የሚገለጥበት መሆን ይገባው የነበረ ቢሆንም በገዢው

ተስፋ አስቆራጭ ስልት ምክንያት የምርጫ ወቅት ሲቃረብ ያልሞት ባይ ተጋዳይነት ደካማ ስልትን እያየን

ይመስላል፡፡ ለወትሮ በተለያዩ ምዕራብ ሀገራት የድጋፍ ስብሳ የሚያዘጋጁ ዲያስፖራዎችም በወያኔ ስትራቴጂ

የተሸነፉ በሚመስል ልኩ ዝምታን መርጠዋል፡፡

ወያኔ በበኩሉ ዲሞክራሲያዊነት፣ ሰላማዊነትና ፍትሀዊነት የነገሰበት ምርጫ ለመቃብሩ እንደሆነ በሚገባ

ስለሚረዳ ካሁኑ ለድምፅ አፈና የተመረጡ ስትራቴጂዎችን በመቀመር ላይ ይገኛል፡፡ ካለፉት 22 የወያኔ አገዛዝ

ዓመታት ተነስተን የደርጅቱን ባህሪ ስንገመግም የምናገኘው ጠቅላይ ሃሳብ ዲሞክራሲያዊነት የጠወለገ ጽጌረዳ

መሆኑን ነው፡፡ ይህ መደምደሚያ ጨለምተኛ እንደማያሰኘኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያለው ተጨባጭ እውነት አገዛዙ

ወደ አፈና መሸጋገሩን የሚያሳይ ነውና፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ የምንጠብቀው ውጤት ካለፈው የተለየ አይሆንም

በሚል ተስፋቢስነት ውስጥ ሊከትን ከወዲሁ ጠንክሮ እየገፋ ነው፡፡

ከምልክቶቹ አንዱና ዋና እንደ ወያኔ ስትራቴጂ የሚወሰደው ተቃዋሚዎችን እያዋከቡ፣ እያሳደዱና እያሰሩ

የህዝብን ሞራል መግደል ነው፡፡ የዚህ አጥፊ ስትራቴጂ ጅማሪ ደግሞ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስራችና

አመራር የነበሩት አቶ አስራት ጣሴ ሆነዋል፡፡ ሰውዬው የተጣበበው የፖቲካ ሜዳ ለማስፋት ገዢውን በመሞገት

ለመቀጠል የወሰኑ መሆናቸው ነው ለግዞት ተላልፈው እንዲሰጡ ያደረጋቸው፡፡ አንደነትን ለመመስረትና በህዝብ

ቅቡል እንዲሆን ያስቻለችው የቀድሞ መሪ ወ/ሪት ብርቱካን የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ስጋት ስለነበረች በስንኩል

ምክንያት መታሰሯን ያስታወሰ የአሁኑ የአቶ አስራት እስር ምክንያትን በሚገባ ይረዳዋል፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች

ሁሉ እንደተለጎመ ፈረስ ወያኔ ካሰመረው መስመር እንዳያፈነግጡ የማስጠንቀቅያ ደውል ነው፡፡

ይህ የወያኔ ድግስ ቀጣይ እንደሚሆን ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ ከአንደነት ፓርቲ እስካሁን ቁጥራቸው

በውል ያልታወቁ አባላቶች ወደ ወያኔ ማጎርያ ካምፕ ተግዘዋል፡፡ በቀጣይም በአመራር ደረጃ የሚገኙ አባላት

ቀናቸውን ብቻ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡ የአረና እጣም የፓርላማ ወንበር ሳይሆን የቂሊንጦ ማጎርያ እንደሚሆን

ከራሱ የወያኔ ካድሬዎች እየተሰማ ነው፡፡

ወያኔ በዚህ የጥፋት ስትረቴጂ ገፍቶ እየሄደና ሀገሪቷን ከማትወጣው ማጥ ውስጥ እየከተታት በመሆኑ ነገ

የማይባልለት ሁነኛ በሆነ የትግል ስትራቴጂ ሊፈተንና ቢቻል ስልጣኑን እንዲያስረክብ አልያም ወደ ልቦናው

እንዲመለስ ማድረግ የተገባ ነው፡፡

ያለመታደል ሆኖ በስልጣን መንበሩ ላይ ያለው ፓርቲ ማህበራዊ እኩልነት፣ ፍትሀዊነት፣

ዲሞክራሲያዊነትና ብሄራዊ አንድነትን ለመፍጠር የተሰጠውን እድል ባለመጠቀሙ ሃላፊነቱ ጠቅላላ በተቀናቃኝ

ፓርቲዎችና በሀገር ወዳድ ግለሰቦች ትከሻ ላይ አርፏል፡፡ እነዚህ አካላት ትልቁን ሀገር የሚል ስም ከፊታቸው

በማስቀደም የ%Eሊት እየተንደረደረ ያለውን ሀገራዊ ህልውና በህብረት ሊታደጉት ይገባል፡፡ ለዚህም ቀጣዩን

ምርጫ ቢያንስ እንደ መንደርደሪያ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ምን እናድርግ?

አዲስና የተለየ ስትራቴጂ ኖሮኝ አልመጣሁም፡፡ ነገርግን ይህች አገር ህልውናዋ ፈታኝ ሁኔታ

ውስጥ እየገባ እንደሆነ በመረዳት፤ ተፈትነው ባዋጡ እና አለማቀፍ ተቀባይነት ባገኙ፤ እንዲሁም በእጃችን

ያሉ፤ቅቡል የሆኑና ሊደረጉ የሚችሉ የትግል ስልቶችን መውሰድ መጀመር ይኖርብናል፡፡

ዲሞክራሲያዊነትን፤ ማህበራዊ እኩልነትን ፍትህን ከማንም ሳይሆን ከራሳችን የትግል አዝመራ የሚገኝ ፍሬ

ማድረግ ይገባናል፡፡ ለዚህም በጀብደኝነት፤ ነፃነትን በመናፈቅና ተስፋ ባለመቁረጥ መታገል፡፡

ዲሞክራሲያዊነት፤ የህይወት፤ የንብረትና ደስታን የመጎናፀፍ እሴቶችን ያነገበ መሆኑን በመረዳትና በማስረዳት

የትግሉን አፅናፍ ማስፋትም በመሪነት ደረጃላይ ካሉ ታጋዮች ይጠበቃል፡፡

ይህ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብትና ክብር የሚያጎናፅፈንን ተግባር ከግብ ለማድረስ ፍፁም

ጀብደኝነት ያስፈልጋል፡፡ ጀብደኝነታችን ብረት አንግቦ ወያኔ በሚወደው ቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ

በሚጠላው ሠላማዊነት፤ እውነታዊነት፤ፍትሃዊነት፤ እንዲሁም ከፍርሀት ቆፈን ነፃ መውጣትና ህዝባዊነትን

በማንገብ ነው ልንገጥመው የሚገባን፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ወያኔ ፍርሀት ውስጥ እንዲገባ የሚያስገድደው ዋና

መንገድ ይኸው ነው፡፡

የትኛውም ትግል ተስፋን አይቆርጥም፡፡ ሁሉን አቀፍ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊነትን የሚመኝ ትውልድ

በተስፋ ይጓዛል፡፡ የማዴባ አገር ሰዎች አፓርታይድን ለመናድ ሲነሱ ‹‹የትግሉ አንድ አካል ተስፋ እንዳለ

ማመን ነው›› ይሏት ነገር ነበረቻቸው፡፡ ይህች ብሂል ዛሬ ለኛ ትሰራለች፡፡ ታስረን፣ ተሰደንና በውርደት

ተይዘን ዘላለም አንኖርም፡፡ የውርደት ደበሎን በክብር ካባ ለመለወጥ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ግድ

ይለናል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ታጋዮች የሚገባቸውን ክብርና ድጋፍ በመለገስ፤ በውጭ ያለነውም ግፊታችንን

በመንግሥት ላይ በማጠናከር ከአገዛዝ ነፃ ለመውጣት በአንድነት መጓዝ ይገባናል፡፡ ከብሄር፤ ከሃይማኖትና

ከመሳሰለው ልዩነት ይልቅ በውርደት የተያዘው ሰውነታችን ይበልጣልና፡፡

ስለዚህም ነው ቆራጥ፣ ጀብደኛ፣ ተስፈኛና ዲሞክራሲያዊ አመራሮችን በማፍራት ካልሆነ በቀር

ዲሞክራሲያዊት ምድር መገንባት አንችልም ስል የምከራከረው፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው እምነት ተስፋና

ፍቅር ነው፤ የወያኔን አጥፊ የምርጫ ድግስ የሚንደው፡፡ ተስፋችን ዲሞክራሲያዊነት፤ እምነታችን ማሸነፍ፤

የአንድነታችን ቋንቋ ፍቅር ከሆነ ከማሸነፍ ደግመን ደጋግመን ከማሸነፍ የሚያግደን አንዳች ኃይል

አይኖርም፡፡

ቸር ይግጠመን

Posted By Alemayehu Tibebu