Archives

የወያኔ ቅዠት

By Arsema Berhanu/Germany/

Arsema

ለወያኔ ውሸት ማለት እውነት ናት፡፡ ለወያኔ እንደእውነት የሚመርና የሚያቅር ነገር የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለወያኔ እንደሀሰት የሚጣፍጥ ምንም ነገር የለም፡፡ ወያኔ የሀሰት የህግ ባል ነው፤ የሚለያዩት ወይም የሚፋቱት ከሁለት አንድኛቸው ወይም ሁለቱም ሲሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሀሰት ግን እስከዓለም ፍጻሜ ስለምትኖር ወያኔ ካልጠፋ ከውሸታምነቱና ከሀገር አጥፊነቱ ተፈጥሯዊ ባሕርይው ሊፋታ አይቻለውም፡፡ ታሪክ ግን ሥራውን የማይረሣ ቆፍጣና ገበሬ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ እነዚህን ጉግማንጉጎች ወደማይቀረው መቃብራቸው እንደሚሰዳቸው የታመነ ነውና መፍረስ የጀመረው የበሰበሰ ሥርዓታቸው ከነሰንኮፉ ተገርስሶ ሀገራችን በቅርቡ ነጻ እንደምትወጣ በሙሉ ልብ አምናለሁ፡፡ በዚህች መንደርደሪያ ወደሰሞነኛው የበረከት ስምዖን ውሽከታ እንለፍ፡፡

redwan_bereket

“የኢትዮጵያ አርሶ አደር እስካሁን በተደረገለት ሥራ በሚገባ የረካ ስለሆነ ‹መንግሥት ሰልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ መንግሥት ተኛ ቢለው ይተኛል፤ ግፍ ብንፈጽም እንኳን አርሶ አደሩ ይህንን መንግሥት ይሸከመዋል እንጂ ምንም አይለውም፡፡”

ይህን የብፃይ በረከት ንግግር በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ባወጣው አንድ ጥናታዊ ዘገባ ላይ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ አሥር ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷና በተጓዳኝም ይህቺው ኢትዮጵያ – ይህቺው ወያኔን በጫንቃዋ እንደምትሸከም በረከት አፉን ሞልቶ የመሰከረላት ጉደኛዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠኔ ጓዙን ጠቅልሎ ከመሸገባቸው አምስት የመጨረሻ ድሃ ሀገራት ውስጥ መመደቧ ነው – (በረከት ይህን ሪፖርት ሳያነብ መሆን አለበት ያን በህልሙ የደረሰውን ጅሎችን የማሞኛ ተምኔታዊ(utopian) ቧልታይና ድንቃይ ድርሰቱን የደሰኮረው!)፡፡ በነገራችን ላይ በአምባገነንነትና በድህነት በወያኔ መንግሥት ሳይቀር የምትታማዋ ኤርትራ በነዚህ ዘገባዎች አልተካተተችም(እንዲያውም ዘገባው ኢትዮጵያን ይግረማት ብሎ ከአሥሩ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኤርትራ እንደሆነች የገለጠ መሰለኝ)፡፡ ኢትዮጵያ ቻድን ብቻ በልጣ በአፍሪካ በርሀብተኝነት ሁለተኛ ስትወጣ ኤርትራ ከአምስቱ የባሰባቸው ሀገራት ውስጥ አልገባችም፡፡ የርሷ መግባት አለመግባት የኔ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህች በማዕቀብና በልዩ ልዩ የማሰቃያ መንገዶች የተወጠረች የቀድሞ የኢትዮጵያ ግዛት ከኢትዮጵያ የተሻለች መሆንዋን በመረጃ በተደገፈ ዘገባ የሚረዳ ጤናማ ሰው የወያኔን ሚዲያ አስችሎት እንዴት ሊከታተል እንደሚችል ይታያችሁ፡፡ ክርስቶስ ‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ› አለ፡፡ ወያኔም ይህችን የክርስቶስ አባባል ቀምቶ በማንሻፈፍ ‹አፌን በሀሰትና ዕብለት እከፍታለሁ› አለና ነጋ ጠባ የማያቅመን የሀሰት ወሬ የማይነጥፍበት አስገራሚ ፍጡር ሆነ፡፡

መዋሸት የማይሰለቸው ‹ልማታዊው መንግሥታችን› በሚዲያው የሚያሳየን ኢትዮጵያና እኛ በግልጥ የምናያት ኢትዮጵያ ተለያይተውብን ተቸግረናል፡፡ እነሱ ‹ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እየተመመች ናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት በየፈርጁ የምናካሂደው የልማት ግስጋሴ ግቡን እየመታ ነው፤ የኢትዮጵያ ልማት ማንም በማይወዳደረው ሁኔታ ወደፊት እየተምዘገዘገ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በማይነቃነቅ ዓለት ላይ ገምብተናል፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሳይሸራረፍ የተከበረባትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት እውን የሆነባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተፈጥራለች፡፡ አሁን ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ እሱንም እየተዋጋነው ነው…›እያሉ በቲቪያቸው እያላገጡብን ነው – ድህነትን ለመዋጋትና ለማሸነፍ ደግሞ ስንት አሥር ዓመቶች እንደሚያስፈልጉን እነሱው ናቸው የሚያውቁት፤ ለመልካም አስተዳደር እኮ አንድ የመኸር ወቅትም ትልቅ ጊዜ ነው – እንኳንስ 23 ዓመታት፡፡ ወያኔዎች ግን በድህነት ላይ እንደዛቱና ወደታሪክነት እንለውጠዋለን እንዳሉ ሦስት ዐሠርት ዓመታትን ሊደፍኑ ነው፤ አያፍሩም፡፡ በማከያው ግን ዕድሜ ለወያኔው ጉጅሌ በምግብ “ሞልቶ መትረፍረፍ” ከአፍሪካ አንዲት ሀገር ብቻ በልጠን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን የተንጣለሉ የአስፋልት መንገዶችንና በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ኢንቬስተሮች የገነቧቸውን ሕንፃዎች “እየተመገቡና እየጠገቡ” መሆናቸው እየተነገረን ነው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ዜጎቻችንም ከዬቆሻሻ ገንዳዎች የሀብታም ፍርፋሪና የሙዝ ልጣጭ ለመሻማት ቀን ከሌሊት ሲራኮቱ ይታያሉ፡፡ የወያኔ ዕድገት ይህ ነው፡፡ የወያኔ ‹ልማታዊ ጋዜጠኞች›ም በበኩላቸው የሕዝቡን ሰቆቃ እንዳይመለከቱና እንዳይዘግቡ እንደአቃቂ ፈረስ ዐይኖቻቸውን

5692303075_16dac64256_m

በወያኔ ተከልለው በብድርና በዕርዳታ በተገነቡ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ካሜራዎቻቸውን በመደቀን ሌት ከቀን በተመሳሳይ ዜናዎችና ሀተታዎች ማደንቆራቸውን ተያይዘውታል፡፡ እኛን እሚያሳክከን ሆዳችን ላይ እነሱ እሚያኩልን እግራችንን፡፡ የሚገርሙ ጋዜጠኞችና የሚገርም የማፊያዎች መንግሥት፡፡

ወደበረከት ንግግር እንመለስ፡፡ እንደእውነቱ በረከት ከፍ ሲል የተናገረውን ነገር ለምን እንደተናገረው አልገባኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለገ ለመረዳት አስተርጓሚ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡  አማርኛ ቋንቋን አውቃለሁ ብዬ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን የበረከትን ንግግር እንደመሰለኝ ተርጉሜ እንዲገባኝ ጥረት አደረግሁ እንጂ በቅጡ ልረዳው አልተቻለኝም፤ እርሱም ቢሆን ጎንደር ውስጥ ብዙ ዓመታትን ስለኖረ አማርኛን ከአፍ መፍቻው ባልተናነሰ ያውቃል ብዬ እገምታለሁና ‹ምን ማለት እንደፈለገ ሳይገባው እንዲህ ያለ የተወነዣበረ ንግግር በአደባባይ ተናግሮ የሰው መሣቂያ ለመሆን አይደፍርም› ብዬ ለማመንም በጣም ተቸገርኩ፡፡

ይህን ንግግር በብዙ መልኩ መገንዘብ እንደሚቻል አምናለሁ፤ በአማርኛው “የጊዮርጊስን ግብር የበላ ሳይነኩት ይለፈልፋል” ወይም በሌላ ፈሊጣዊ አገላለጽ “የምላስ ወለምታ” የምንላቸው ምሥል ከሳች አባባሎች አሉ፡፡ በፈረንጅኛው “Fruedian slip” የሚባል በሥነ ልቦና የትምህርት ዘርፍ የሚጠቀስ ሐረግ አለ፡፡ ይህ ሰው የተናገረውን ከነዚህ ጽንሰ ሃሳባዊ ዕይታዎች አንጻር ብንመለከተው ወያኔ ከመጃጀቱና በወንጀል ድርጊቶች ከመጨመላለቁ የተነሣ ነፍሱ እየቃዠች መሆኗን መረዳት አያዳግተንም፡፡ አለበለዚያ ግፍ በመሥራት ላይ የቆመ የወሮበሎች መንግሥት  “ገበሬው ግፍ ብንፈጽምበትም ይሸከመናል” ብሎ መናገሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አንድ ጤነኛ ሰው ከመሬት ተነስቶ “በጥፊ ባጮልህና ዐይንህን በጉጠት ባወጣውም እንደማትቀየመኝ አውቃለሁ! ከኔ በበለጠ ሊያሰቃይህ የሚችል ወገን እንደሌለ ስለማውቅ ለስቃይ ለስቃይ እኔው እሻልሃለሁና ምርጫህ እኔው ብቻ ልሆን ይገባኛል” ብሎ እንዴት ሊናገር ይችላል? እንዲህ ብሎ የሚናገር ሰው ካለ ደግሞ እንደበረከት የለዬለት በሽተኛ እንጂ ጤናማ ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ከወፈፌና በሽተኞች ንግግር ይሠውረን፡፡ “ዱባ ካላበደ ቅል አይጥልም” አሉ? የሚገርም በረከት ነው የሆነብኝ እባካችሁን፡፡

ይህን ንግግር በቁሙ መረዳት እንደሚቻለው በረከት ማለት ቅል ራስና እሚናገረውን እንኳን የማያውቅ ገልቱ ሰው ነው፡፡ ለመደዴ የቃላት አጠቃቀሜ ይቅርታ ይደረግልኝና እንደዚህ ያለ ድፍን ቅልና ባልጩት ራስ የኢትዮጵያ አንዱ ባለሥልጣን እንደነበረ በነገው የታሪክ መዝገባችን ሠፍሮ ሲታይ በቀጣይ ትውልዶቻችን ዘንድ በእጅጉ ከምናፍርባቸው የታሪክ ስብራቶቻችን መካከል አንዱና ትልቁ ነው፡፡ ሰው ምን ቢጃጃል እንደዚህ አይናገርም ወይም አይጽፍም፤ አለበለዚያም አብዷል ማለት ነው፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” የሚባለው እኮ እንደዚህ ያለ በደናቁርት አስተሳሰብ የተለወሰ የአነጋገር ጭቅቅት ሲያጋጥም ነው፡፡ ተመልከቱልኝ፡-

“መንግሥት ሠልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ ተኛ ቢለው ይተኛል፡፡”

ምን ማለት ነው? ገበሬውን በማስገደድም ይሁን በማታለል ሠልፍ ማስወጣት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው እንደሕጻን ልጅ ገበሬውን በትዕዛዝ አባብሎ ማስተኛት የሚቻለው? ምን ዓይነት ዕብሪትና ትምክህት ነው? ምን ዓይነት የድንቁርና አነጋገር ነው? ለነገሩ ወያኔዎች ከአለቃቸው ከመለስ ጀምሮ ለአነጋገራቸው ደንታ የላቸውም፤ የሚያስቡት እንደጤናማ ሰው በጭንቅላት ሣይሆን እንደ አውሬ በጡንቻ ሣይሆን አይቀርም – አውሬ በጡንቻው ካሰበ፡፡ ሀገር፣ ታሪክና ወገን አለን ብለው ራሳቸው ስለራሳቸው የሚያምኑ አይደሉም፤ ባህል የላቸውም፤ ሞራል ወይም ‘ethical values’  ብሎ ነገር አያውቁም፤ ምናልባት ከሴቴኒዝም በስተቀር ሁነኛ ሃይማኖትም ያላቸው አይመስሉም (ለዚህም ይመስላል ወንጀለኝነት የሚያዝናናቸውና በሰዎች ስቃይ የሚደሰቱት)፤ በትውፊትና በወግ ልማድ አያምኑም፤ ባጭሩ ወፍዘራሽ የመርገምት ውጤቶች ናቸው፡፡ ከሁሉም ነገር የወጡና ከዜሮ መጀመር የሚወዱ በፈረንጅኛው አገላለጽ nihilists ናቸው – hedonist የሚል ምርቃትም ማከል ይቻላል፡፡ ታሪክን ማጥፋትና ነባር ባህልን ማውደም ያረካቸዋልና፡፡

ወያኔዎች ማለት ባጭሩ ማሊ በምትባለዋ አፍሪካዊት ሀገር ‹አዛዋድ› በሚል ራሳቸው በፈጠሩት አዲስ ግዛት ውስጥ ፈረንሣይ ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋቸው ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በሼሪዓ ህግ የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት መሥርተው እንደነበሩት የቱዋሬግ አማፅያን  የሚመሰሉ ናቸው – ወያኔዎች እንደሶማሊያው አልሻባብ ዓይነትም ናቸው – ነገር ግን መንግሥት ስለያዙ ደፍሮ በአሸባሪነት የፈረጃቸው ዓለም አቀፍ ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለነገሩ ወያኔዎች ሀገራዊ አጀንዳ ስለሌላቸውና የማንንም ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ አጀንዳ አንከርፍፈው በተባባሪነት ስለሚጓዙ ለዓለም አቀፍ ታዋቂ ኃይሎች እስትራቴጃዊ ጠቀሜታ እስከሰጡ ድረስ በአጋርነት የሚያስጠጋቸውና ሙሉ ድጋፍ የሚሰጣቸው አያጡም(ኢትዮጵያውያንን ለጊዜውም ቢሆን እያስቸገረን ያለው ይህን መሰሉ የወያኔ እስስታዊ ተፈጥሮ ነው)፡፡ እነዚያ የአልቃኢዳ የአፍሪካ ክንፍ የሆኑ አማጽያን በቲምቡክቱ ውስጥ የነበሩ ዕድሜያቸው በሺዎች ዓመታት የሚገመት የታሪክ ቅርሶችን በዶማና አካፋ እንዲሁም በግሬደር በአጭር ጊዜ የሥልጣን ቆይታቸው ውስጥ ድራሻቸውን ማጥፋታቸውን የቅርብ ጊዜ ትዝታ በመሆኑ ከዐይነ ልቦናችን ገና አልተሰወረም፡፡ ወያኔዎችም እያዋዙ በእስከዛሬው የኃይል አገዛዛቸው እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶችንና ታሪኮችን አጥፍተዋል – ከሁሉም የሚብስ ጥፋታቸው ግን ከቁሣዊው ይልቅ ሥነ ልቦናዊውና  ኅሊናዊ ወመንፈሣዊው አጠቃላይ ውድመት የበለጠ ኪሣራ ያደረሰብንና ለማገገምም ብዙ ጊዜ የሚወስድብን ከባዱ ጥፋት ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ጅብ እማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንደሚል በምናውቃቸው ምሥኪን ዜጎች መሀል ሆነው ገበሬው የነሱ እንደሆነ የሚሰብኩን፡፡ ለነገሩ ጅብ እንኳን በማያውቁት ሀገር ነበር ተናገረው የተባለውን የተናገረው፡፡ ወያኔዎች ግን ዐይናቸውን በጨው አጥበው እኛው ፊት ሸፍጣቸውንና የሀሰት ቱሪናፋቸውን ካለተቀናቃኝ ለብቻቸው በተቆጣጠሩት ሚዲያቸው ያናፉብናል፡፡

በማጠቃለያዬ ማሳሰብ የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ በረከትም ሆንክ ሌላ ጊዜ ሰጠኝ የምትል ባለሥልጣን ሁሉ ካለፈው ታሪክ ተማር፡፡ የሚያሳዝነኝ ነገር አፄዎቹ ከቀደሙት አፄዎች መማር ሳይፈልጉ ቀሩ፤ ቀሩናም ሕዝብን ሲንቁ ሲንቁ ቆይተው በናቁት ሕዝብ እርግማንና አመፅ ምክንያት እንዳልሆኑ ሆኑ – ዘር እንኳን አልወጣላቸውም፡፡ ደርግም ፈጣሪን ሣይቀር ከድቶና አስከድቶ ራሱን የፈጣሪን ያህል በመቁጠር ሕዝብን ሲንቅና ሲያዋርድ ቆይቶ በናቀውና ባዋረደው ሕዝብ እርግማንና ሁለንተናዊ የእምቢታ አመፅ ሰበብ እንደባቢሎን አይሆኑ ሆኖ ተንኮታኮተ – ስንትና ስንት ዘመናዊ ትጥቅ እያለው አንዱም አላዳነውም፤ ይንቃቸው በነበሩ መናኛ የጫካ ወሮበሎች በቀላሉ ተገፍትሮ ወደቀ፡- መጽሐፉ ‹ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም› እንደሚል መዘንጋት አይገባም፡፡ እነዚህኞቹ ፀረ-ኢትዮጵያ ጉጂሌዎችም አይነጋ መስሏቸው የኢትዮጵያ ታሪክ መዝገብና ሕዝቡ ሊሸከሙት ያልተቻላቸው ግፍና በደል በሀገርና በሕዝብ ሠሩ፤ ዋናዎቹ የአገዛዙ ቁንጮዎች በሣምንታት ልዩነት ወደማይቀሩበት የሲዖል ሥፍራቸው ተጓዙ፤ ቀሪዎቹም በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ተሰንቅረው ያደርጉትን በማጣት ፈጣሪ ሩህያቸውን ጨርሶ እስኪወስዳት እየተንጠራወዙ ይገኛሉ – ይህን እውነት ማስተሃቀር ፈጽሞውን የሚቻል አይደለም፡፡ ለውስጥ አዋቂዎች ወያኔዎች በሕይወት እንደሌሉ ከገባን ቆይተናል፡፡ በሕይወት ያሉ እንዲመስሉ የሆነው ምናልባት ለበጎ ነው፡፡ እንጂ እንደእውነቱ ወያኔ አከርካሪው የተመታው ዋናውን የሥርዓቱን መሃንዲስ መለስ ዜናዊን ፈጣሪ ባልተጠበቀ ወቅት ገና በ‹ማለዳ ዕድሜ›ው ሲጠራው ነው፡፡ ልብ ከተገኘ “ሁሉም ከእያንዳንዱ፣ እያንዳንዱም ከሁሉም እንዲማር ጊዜ ለመስጠት ተብሎ ነው የወያኔ የማይቀር ኅልፈት አዝጋሚ እንዲሆን የተደረገው” ብሎ ማሰብም ይቻላል – ምንም ነገር ማሰብ በማንም አልተከለከለምና (ወያኔዎች ግን ይህንንም ተፈጥሯዊ መብት ሊነፍጉን ይቃጣቸዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርክ ወያኔን ስለመጣል ወይም በሀገሪቷና በሕዝቡ ላይ የጣሉትን ግፈኛ የአገዛዝ ቀምበር ስለመቃወም “ማሰብ”ም አትችልም – ማሰብህ በዐይነ ውኃህ የፊት-ንባብ ከተደረሰበት በአሸባሪነት ተጠርንፈህ ዘብጥያ ትወርዳለህ)፡፡ ማሰብ በቻልንበት ሃሳብ ውስጥ በጊዜ ሰጪነት የምንጠረጥረውን አካል ደግሞ ለሁላችንም እኩል በሚገባን ቋንቋ አቶ ታሪክ ልንለው እንችላለን፡፡ ታሪክ የሚያዳላ ይመስለናል እንጂ ለማንምና ለምንም በጭራሽ አያዳላም – የራሱ የጊዜ ቀመር እንዳለው ግን ማጤን ተገቢ ነው (እርግጥ ነው – ‹መብሰሉ ለማይቀረው ጭንቅላት እንጨት ይፈጃል› እንደሚባለው አንድ ታሪካዊ ኹነት ተከናውኖ ቀጣዩ ሌላ ኹነት እስኪከናወን የሚኖረው የጊዜ እርዝማኔ በትግስታችንና በሃይማኖታችን ጭምር አሉታዊ ጥላውን ማጥላቱ የማናልፈው የዘመን ቅጣት ይመስላል፤ ዕድሜ ይስጠን ሁሉን እናያለን፡፡ ሰላም ያገናኘን