Archives

የግል መጽሔት አዘጋጆች፤ “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” መባላቸውን አጣጣሉ

2b19039892926da39539af655fbfaff8_M

  • Written by  አበባየሁ ገበያው

ሪፖርቱ የአደጋ ምልክት ነው ብለዋል

“በኢትዮጵያ የሚታተሙ ሰባት የግል መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሳናት ሆነዋል፤ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ ያደርጋሉ” ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያሠሩት የጥናት ሰነድ አመለከተ። የመጽሔቶቹ አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ሪፖርቱን ያጣጣሉ ሲሆን ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡ ተቋማቱ ያስጠኗቸው አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁና ሊያ መጽሔቶች ሲሆኑ ከመስከረም 1 ቀን እስከ ህዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ባወጧቸው ህትመቶች ላይ በተደረገ የአዝማሚያ ትንተና መሠረት፤ መጽሔቶቹ የግል መገናኛ ብዙሃን ሳይሆኑ የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል ተብሏል፡፡ መጽሔቶቹ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ይዘት፣ ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉና የቀለም አብዮት ባስተናገዱ አገሮች የታየውን ቅኝት የሚከተሉ ሆነው ይታያሉ ብሏል – የጥናት ሰነዱ፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ የጥናት ሰነዱን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ “የሁሉም ጽሑፎች ይዘት ያተኮረው አሉታዊ ጉዳዮችን በማራገብ፣ መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ፣ መንግስት በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲ መስኮች ያመጣቸው ለውጦች የሌሉ በማስመሰል እንዲሁም ህዝቡ ከችግር ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ላይ በማሾፍና በማንኳሰስ ነው” ብሏል፡፡

ሁሉም መጽሔቶች የጋራ የመረጃ ምንጮችን ይጠቀማሉ ያለው ሰነዱ፤ የኒዮሊበራል አክራሪ ሃይሎች ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች፤ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው የድሮ ስርአት ናፋቂዎችና በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ሲል ዘርዝሯቸዋል፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ የወጣውን የጥናት ሪፖርት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የግል መጽሔቶች አዘጋጆች፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል” በሚል የወጣውን ትንተና ያጣጣሉት ሲሆን ጥናቱ ከዚህ ቀደም በታየው ልምድ መሠረት ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት መጽሔቶች መካከል የእንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ኤልያስ ገብሩ፤ “ጥናቱ የግሉን ፕሬስ ሆን ብሎ ለማሸማቀቅ እና ለመወንጀል የወጣ ነው” ሲል ተችቶታል፡፡

የጥናቱ ምንጭ የሆኑት ሁለቱ ተቋማት የመንግስት እንደመሆናቸው ገለልተኛ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ ብሏል አዘጋጁ። “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” የሚለው አገላለጽ በየአስራ አምስት ቀኑ የምትወጣውን “ዕንቁ” መጽሔትን አይወክልም፤ እኛ ከጋዜጠኝነት መርህ አኳያ እንሠራለን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለንም፤ ልንሆንም አንችልም ብሏል – ዋና አዘጋጁ፡፡ “ነገር ግን መንግስት አካሄዱን እንዲያስተካክል በመረጃ ተደግፈን እንተቻለን፣ የምንሠራው ህግና ስርአቱን አክብረን ነው” ሲል ገልጿል፡፡ ሪፖርቱ ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን የጠቀሰው ዋና አዘጋጁ፤ በተለይ መጽሔታቸውን ከሽብርተኝነት ጋር ማያያዙና የአመጽ ጥሪ አቅራቢ እያለ መወንጀሉ በስራቸው ላይ ከባድ ስጋት እንደሚፈጥርባቸው ገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት ያቀርቡ የነበሩ ጋዜጦችም የዚህ መሰሉ ውንጀላ ሠለባ ከሆኑ በኋላ ነው የተዘጉት ያለው ኤልያስ፤ የአሁኑ ሪፖርትም በመጽሔቶቹ ላይ ትልቅ አደጋ እንደተደቀነ የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡

ከሰላሳ በላይ ገፆች ያሉትን የጥናት ሪፖርት እንዳነበበ የገለፀው የ “ቆንጆ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ካሣ በበኩሉ፤ መንግስት በቀጣዩ ምርጫ መጽሔቶች ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ በመፍራቱ ነው እንዲህ ያለ ሪፖርት ያወጣው ሲል ተናግሯል፡፡ መጽሔታችን ሚዛናዊነትን ጠብቆ የጋዜጠኝነት ሚናውን እየተወጣ እንጂ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለም ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ መንግስት የግሉ ፕሬስ ስላልተመቸው በርግገው ከሃገር ይሰደዳሉ በሚል እምነት ነው ይሄን ያደረገው ብሏል፡፡ በተለይም የአጥኝዎችን ማንነት ስንመለከት ዋና ስራቸው ዜናዎችን መቀበልና ማሠራጨት እንጂ ጥናት እያጠኑና እያስጠኑ፣ ደረጃ እንዲመድቡ ወይም እገሌ መጽሔት ይሄን ያህል በመቶ ሽብርተኝነትን ቀስቅሷል፣ ይሄን ያህል በመቶ ደግሞ የኢኮኖሚ እድገቱን ክዷል በሚል መፈረጅ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ጋዜጦች የከሰሙበትን መንገድ ሲያስታውስም፤ “ብዙውን ጊዜ በአዲስ ዘመን ላይ ትችቶች በተከታታይ ይቀርባሉ፣ በቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ይሰራበታል፤ ከዚያም የህዝብ አስተያየት ተብሎ ይሰበስብና ይወገዛል፤ በሂደትም መጽሔቶቹንና ጋዜጦቹን በተለያዩ ክሶች በማዳከም እንዲከስሙ ይደረጋል” ያለው ቴዎድሮስ፤ ይህ መሰሉ ልምድ ባለበት ሁኔታ የዚህ ሪፖርት መውጣት ከፍተኛ ስጋት ይፈጥርብናል ብሏል፡፡

“ጥናቱን ያደረጉት የመንግስት ተቋማት ምን ለማለት እንደፈለጉ ይገባናል፤ እዚህች ሃገር ላይ የፕሬስ ነፃነት እንዲኖር አይፈልግም” ያለው የሳምንታዊው ሎሚ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ የጥናቱ ሪፖርት በግል መጽሔቶቹ ላይ እርምጃ ሊወሰድ መታሰቡን የሚጠቁም ነው ብሏል። “መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሣናት ናቸው የተባለው እንደልብ የምናገኛቸውን የመረጃ ምንጮች ስለምንጠቀም ነው” ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ቃለ መጠይቅ ለመስራት ስንሞክር አናገኛቸውም ብሏል፡፡ ጥናቱን የሠሩት ተቋማት እኛን ከመፈረጅ ይልቅ በማተሚያ ቤቶች ያለብንን ችግርና ወረቀት ከውጭ ሀገር ለማስመጣት ያለውን ፈተና ለምን አያጠኑም ሲልም ጠይቋል – ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፡፡ የሊያ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር መላኩ አማረ በበኩሉ፤ በጥናቱ የተገለፀው ፍረጃ የመጽሔታቸውን ባህሪ እንደማያንፀባርቅ ገልፆ፤ ከሪፖርቱ በተቃራኒው የህብረተሰቡ ልሣን በመሆን እየሠሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጥናቱ ሚዛናዊነት የጐደለው ነው ያለው መላኩ፤ ጥናቱ ተደረገ የተባለባቸውን ያለፉትን ሶስት ወራት የመጽሔቶች ህትመት እንዳየና ከተወነጀሉበት “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” አስተሳሰብ የራቁ ጉዳዮችን ሲያነሱ እንደነበር ማረጋገጡን ገልጿል። የፕሬስ ትልቁ አላማው የፖለቲካ አስተሳሰብና የህዝቡን ሃሳብ በነፃነት ማንሸራሸርና ማስተላለፍ ነው ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ሪፖርቱ ምናልባትም የመጽሔቶቹ ቀጣይ ህልውና ላይ ቀይ ምልክት የሚያበራ በመሆኑ አዘጋጆችን የበለጠ የሚያሸማቅቅና ሥጋት ላይ የሚጥል ነው ብሏል። “መንግስት ፕሬሶችን ለማጥፋት ሲፈልግ ቀይ መብራት የሚያሳየው አዲስ ዘመን ላይ በሚወጡ ትችቶች ነው” ያለው መላኩ፤ የረቡዕ እለቱን የጋዜጣውን እትም ለየት የሚያደርገው ርዕሰ አንቀፁም ጭምር የኛ ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ነው ብሏል፡፡ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዮሐንስ ካሣሁን ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያየት፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣን” የሚለው ፍረጃ ለእኛም አዲስና ያልጠበቅነው ስለሆነ ተገርመናል፤ እኛ የምንሠራው የጋዜጠኝነትን ሙያ እንጂ ሌላ አይደለም ብሏል። “ቀደም ባሉት የአዲስ ዘመን እትሞች ላይ ‘አዲስ ጉዳይ’ን የሚያብጠለጥሉ ጽሑፎች ሲስተናገዱ ተመልክተናል፡፡ እኛም ለትችቶቹ መልስ ስንሰጥ ከርመናል፡፡ ይሄኛውም ከዚያ የተለየ አይሆንም” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ በመጽሔቶቹ ላይ የተደረገው ጥናት ያተኮረው “የመንግስት ኀላፊዎችን የግል ስብዕና የሚነኩ፣ የአመጽ ጥሪዎችን የሚያስተላልፉ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ፣ የፖለቲካ ስርአቱን የሚያጨልሙ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚክዱና ህገመንግስቱን የሚያጣጥሉ” በሚሉ ነጥቦች ላይ ሲሆን በተከታታይ ህትመቶች የተነሳበት ድግግሞሽም ሆነ በአንድ ህትመት የተለያዩ አምዶች የተነሳበት ብዛት በቁጥር መተንተኑ ተገልጿል፡፡