Archives

አቶ አንዳርጋቸው አሳልፈው ለወያኔ የተሰጡት በሻእቢያ መሆኑ ተዘገበ

anda

አቶ አንዳጋቸውን አሳልፎ የሰጠው የኤርትራ ደህንነት ጽ/ቤት እንደሆነ ኢትዮጵያ ሪቪዉ ዘገባ። ለሁለት ወራት አደረኩት ባለው ምርመራ ፣ በግንቦት ሰባቱ ዋና ጸሃፊና በኤርትራ መንግስት መካከል የነበሩ አንዳንድ ልዩነቶችን ኢትዮጵያ ሪቪው ዘርዝሯል። አቶ አንዳርጋቸው በሻእቢያ ተስፋ ቆርጠው እርዳታ ከግብጽ ለማግኘት ወደ ካይሮ አመርተው እንደነበረ የዘገበው ኢትዮጵያ ሪቪው፣ የአቶ አንዳርጋቸው የካይሮ ጉዞ ሻእቢያን እንዳበሳጨም ገልጿል።

የሻእቢያ ሰለባ ሲሆኑ አቶ አንዳርጋቸው የመጀመሪያቸው እንዳልሆኑ የዘገበው ኢትዮጵያ ሪቪው የትሕዴን ( የትግራት ህዝብ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ) መሪ አቶ ፍስሐ ሃይለማሪያን በስድስት አመታት በፊት እንደተገደሉ፣ የአርበኞች ግንባር መሪ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህም የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አትቷል።

በጉዳዩ ላይ ግንቦት ሰባት የሰጠው መግለጫ እስከአሁን ባይኖርም፣ ከሳምንት በፊት ዋሺንግተን ዲሲ በተደረገዉ ሕዝባዊ ስብሰባ ፣ የድርጅቱ መሪዎች ከሻእቢያ ጋር ያለው ግንኙነት ቀጣይነት እንዳለው የሚይሳዩ መልሶችን ይመልሱ እንደነበረ በስፋራው የነበሩ ይናገራሉ።

ከአምስት አመታት በፊት አቶ አንዳርጋቸው አስመራ እንደገቡ ኢትዮጵያ ሪቪው ለመጀመሪያ ጊዜ መዘገቡ ይታወቃል። በወቅቱም የድርጅቱ ሊቀመንበር በአዲስ ድምጽ ራዲዮ፣ የኢትዮጵያ ሪቪዉን ዘገባ ለማስተባበል የሞከሩ ቢሆንም፣ ጥቂት ወራት ካለፈ በኋላ፣ አቶ አንዳርጋቸው እራሳቸው፣ በቺካጎ በተደረገ ስብሰባ አስመራ ሄደው እንደነበረ በመገልጽ፣ ኢትዮጵያ ሪቪው ዘግቦት የነበረዉን ዘገባ፣ ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሪቪዉን ዝርዝር ዘገባ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !

የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

 

(የህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
========
የምንወዳት ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያዩ ሥርዓታት ውስጥ የተለያዩ የሰዎችን እስር አስተናግዳለች፤ ዛሬም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
በ97 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮች፣ የግል ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማኅበራት አመራሮች …ታስረው ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት በኋላ በይቅርታ፣ በነጻ …መፈታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጊዜም በኋላ፣ በተለይ አፋኝ በሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ብዙዎች ታስረዋል፣ እየታሰሩም ይገኛሉ፡፡

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና

በዘንድሮ ዓመት ግን የምናየው እስር የተለየ ሆነብኝ፡፡ የሕገ- መንግሥቱን አንቀ ጽ 30 መሰረት በማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላቶቻቸው ለሰልፉ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት እየተያዙ ለቀናቶች ታስረው መፈታት የተለመደ ሆነ፡፡ (ወይ ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ይሄንን እርምጃ ዘንድሮ በደንብ አይተውታል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያኖች፣ ፖለቲከኞችና በርካታ ዜጎች በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል፣ ክስም ተመስርቶባቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቡን በመፈረም የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የፊታችን ቅዳሜ ሜክሲኮ በሚገው የመብራት ሐይል አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ አቅዶ ስድስት አባላቱ ዛሬ ቂርቆስ አካባቢ በመኪና ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ እያሉ መታሰራቸውን ሰማን፡፡
ፖሊስም ‹‹የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ አልያዛችሁም›› በማለት ጥዋት አካባቢ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳሰራቸው እና የፓርቲው አመራሮች በፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመገኘት ከኃላፊዎቹ ጋር ቢነጋገሩም ልጆቹ ቃላቸውን መስጠታቸውንና ፖሊስ ልቀቃቸው የሚል ትዕዛዝ ሲደርሰው እለቃቸዋለሁ ማለቱን ወዳቻችን ዳዊት ሰለሞን በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ አስነብቦን ነበር፡፡
እኔም እንደጋዜጠኛ ጉዳዩን ለማጣራት የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር ወደሆኑት አቶ ሙሴ ሰሙ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ደውዬ እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ እንዲያውም፣ አቶ ሙሼ የተደረገው ነገር አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ በነገው ዕለት በግል መኪናቸው ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዳቸውን አጽንኦት ሰጥተው ነግረውኛል፡፡
እንዲሁም፣ በዛሬው ዕለት በእነሀብታሙ አያሌው የክስ መዝገብ አንድነት ፓርቲ ላቀረበው አቤቱታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በአራዳ ፍርድ ቤት ለማድመጥ በችሎት ተገኝተው የነበሩ ስድስት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት (ዳንኤል ፈይሳ፣ አብነት ረጋሳ፣ ጥላዬ ታረቀኝ፣ ፋሲካ አዱኛ፣ ብርሀኑ ይግለጡና መሰለ አድማሴ) በደህነት ሃይሎች ተይዘው በቶዮታ ደብል ጋቢና ኮድ 3-50559 መኪና ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸውን የፍኖተ ነፃነት የማዕከላዊ ምንጮች ገልጸው ነበር፡፡ ከሰዓታት በኋላም የታሰሩት የፓርቲው አባላት ተፈትዋል፡፡
እስያዊቷ ሀገር ማሌዥያ፣ የመንገደኛ አውሮፕሏኖቿ አንዴ ሲሰወሩ፣ አንዴ ሲከሰከሱና በሮኬት ሚሳይል ሲመቱ ዛሬም ድረስ ደርሰዋል፡፡ በዛሬው ዕለት እንኳን ከሆላንድ አመስተርዳም ወደ ማሌዥያ ኩዋላላምፑር ሲጓዝ የነበረ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን በሮኬት ሚሳይል ተመትቶ (በራሽያ መሆኑ እየተነገረ ነው) በዩክሬን ግዛት በመከስከስ 295 ሰዎች አልቀዋል፡፡ 
በሀገራችን ደግሞ ሁሉን ዓቀፍ የእስር እርምጃ በመንግሥታችን እየተወሰደ መመልከቱ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ነው፣ በርዕሴ ‹‹የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል!›› በማለት የገለጽኩት፡፡
ወዳጄ ዳዊት ሰለሞንም “Ethiopia the land of prisoners” (ኢትዮጵያ የእስረኞች ምድር) የሚል መልዕክት ከአምስት ሰዓታቶች በፊት በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሮ ተመልክቻለሁ፡፡ ማሌዥያ በአውሮፕላን አሳዛኝ አደጋ ጣጣ በዓለም ስትታወቅ እኛ ደግሞ ዜጎችን በገፍ መማሰር እንታወቅ?!
እኔ ደጋግሜ ብያለሁ፣ እስር መፍትሄ አይደለም፡፡ ዜጎችን ማሰር ብዙ የማይገርምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ መንግስታችን ሆይ! ዜጎችን የማሰር ጉዞውን በአንክሮ አስብበት! አሊያ… ከባድ ነው! መዘዝ አለው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! —

በፒያሳ ወርቅ ቤቶች ኮርኒስ ውስጥ ለ3 ቀን ያሸመቀው ወጣት ተያዘዘ

በረሃብ ደካክሞ ለ5ቀን ራስ ደስታ ሆስፒታል ህክምና ተደርጎለታል

lalibela

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ፒያሳ እምብርት ላይ በሚገኘው ዝነኛው ላሊበላ ወርቅ ቤት ውስጥ ለብዙዎች ትንግርት የሆነ ነገር ተከስቷል፡፡ ያውም በጠራራ ፀሃይ፡፡ ላሊበላ ወርቅ ቤት፤ በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ወርቅ ቤቶች ለየት የሚያደርገው ለምሳ ከ7-9 ሰዓት መዘጋቱ ነው የሚሉት የወርቅ ቤቱ ባለቤት አቶ ኢዛና ካሣዬ፤ የዚያን ዕለት ግን ገበያ በመብዛቱ ለምሳ ሳይዘጋ እንደቀረ ይናገራሉ፡፡
የላሊበላ ወርቅ ቤት ትንግርት የተጀመረው ከጎኑ በሚገኘው ኢየሩሳሌም ወርቅ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ኮርኒስ ውስጥ የመንደፋደፍ ድምፅ እንደሰሙ የሚናገሩት የኢየሩሳሌም ወርቅ ቤት ሰራተኞች፤ ለጊዜው ቢደናገሩም “እርግብ ነው” በሚል ተስማምተው ወደ ስራቸው መግባታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም ድምፁ እየጨመረ በመምጣቱ ጥርጣሬ ይገባቸውና አንደኛው ሰራተኛ ክፍት በሆነው ኮርኒስ በኩል ባትሪ አብርቶ ተጠግቶ ይመለከታል፡፡
ኮርኒስ ውስጥ የሚንደፋደፈው እርግብ ሳይሆን ሰው መሆኑን ያረጋገጠው የወርቅ ቤቱ ሰራተኛ፤ “ሌባ… ሌባ” እያለ ሲጮህ ያልደነገጠ የለም፡፡ ኮርኒሱ ውስጥ ያሸመቀውን ወጣት ጨምሮ ሁሉም ድንብርብሩ ወጣ፡፡ ለማምለጥ የሞከረውም ወጣት ሲንደፋደፍ ከጎኑ ያለው የላሊበላ ወርቅ ቤት ኮርኒሱ ተቀዶ መሬት ሊፈጠፈጥ ሲል አንዱ የእንጨት ምሰሶ ደግፎት ይተርፋል፡፡  በዚህ ዱብዕዳ ወርቅ በመግዛት ላይ የነበሩ ደንበኞችና የወርቅ ቤቱ ሠራተኞች መደናገጣቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ግርግር ወጣቱ ተመልሶ ወደ ኮርኒሱ  ውስጥ ይሸሻል፡፡ ይሄኔ ሁሉም ባለወርቅ ቤት በየራሱ ኮርኒስ ውስጥ ባትሪና ሻማ ይዞ በመግባት ወጣቱን ተጠርጣሪውን ማደን ጀመረ ይላል፤ የቅዱስ የብር ጌጣጌጥ መሸጫ ቤት ሠራተኛ ብርሃኑ አበበ፡፡ ተርታውን ያሉት የወርቅ መሸጫ መደብሮች የጥንት ቤቶች ስለሆኑ በኮርኒሳቸው ውስጥ ለውስጥ እንደሚገናኙ የነገሩን ሠራተኞቹ፤ ማታ ማታ ቤቱን ከመዝጋታቸው በፊት ወርቅና ብሮቹን ካዝና ውስጥ ከተው እንደሚቆልፉባቸው ገልፀዋል፡፡
በየግል ተጀምሮ የነበረው ወጣቱን የማደን ዘመቻ ከደቂቃዎች በኋላ በፖሊስ ሃይል ተጠናክሮ ቢቀጥልም ወጣቱ እምጥ ይግባ ስምጥ ሊታወቅ አልቻለም – ይላሉ አቶ ኢዛና፡፡ ከዚያም ጣራው አናት ላይ ወጥተው አሰሳውን ቀጠሉ፡፡ ወጣቱን ባያገኙትም ስለእሱ ድርጊቶች የሚጠቁሙ ፍንጮችን ለማግኘት እንደቻሉ የሚናገሩት አቶ ኢዛና፤ አንድ ቦታ ላይ ጣራው መቀደዱን ማየታቸውን፤ እዚያው አካባቢም ጣራው የተቀደደበት መቀስ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ወዲያው የተቀደደውን ቆርቆሮ በባለሙያ እንዳስደፈኑ ጠቁመው፤ አሰሳው ግን ያለውጤት መቋጨቱን ተናግረዋል፡፡
በነጋታው አርብ ጠዋት ደግሞ ቅዱስ የብር ጌጣጌጥ መሸጫ መደብር ውስጥ ሌላ ፍንጭ ተገኘ፡፡ በሩን ለመክፈት ሲሞክር የበሩ ቁልፍ (ጋን) እንዳስቸገረው የሚያስታውሰው ብርሃኑ፤ የቤቱን ባለቤት ጠርቶ አብረው ከፍተው መግባታቸውን ይገልፃል፡፡ ውስጡን ሲቃኙም አንዳንድ ነገሮች ተመሰቃቅለው ያገኛሉ፡፡ ወዲያው ፖሊስ ይጠሩና ሌላ የፍለጋ ዘመቻ ይጀመራል፡፡ ሆኖም ተፈላጊው አልተገኘም፡፡
ቅዳሜ ጠዋትም ብርሃኑ ከሱቁ ባለቤት ጋር ነበር በሩን የከፈትነው፡፡ የብር ጌጦቹን የሚደረድርበትን የመዝጊያ ብረት ሸርተት ሲያደርግ ነው ፈፅሞ ካልጠበቀው ነገር ጋር የተፋጠጠው፡፡ ሁለት ቀን መከራቸውን ያበላቸው ወጣት፤ ትልቅ የብር መስቀል በእጁ ይዞ መስተዋቱ ጋ ተለጥፎ ቆሟል፡፡ “ፊት ለፊት ቢያገኘኝ ግንባሬን ብሎኝ ወደ ውጭ ለመፈትለክ አስቦ እንደነበር ያስታውቅበታል” ያለው ብርሃኑ፤ በመስተዋት ውስጥና ውጭ ሆነን እንፋጠጣለን ብሎ የጠበቀ አይመስልም ብሏል፡፡ በሩን ከፍተው ሲገቡ ወደ ውስጥ ሊያመልጥ ቢሞክርም ወዴትም ሳይደርስ እንደያዙት የሚናገረው ብርሃኑ፤ ወዲያው  ተዝለፍልፎ መውደቁንም ገልጿል፡፡ ሰውነቱ ደካክሞና አቅም ክዶት እንደነበር በመግለፅም የምግብ እጥረት ሳያጋጥመው እንዳልቀረ ግምቱን ገልጿል፡፡
ወጣቱ ኪሱ ሲፈተሽ የብር ጌጦችና ጥቂት የወርቅ ቀለበቶች የተገኙበት ሲሆን ጀርባው ላይ ባዘለው ቦርሳ ውስጥ ደግሞ ውሃ፣ ቆሎ፣ መቀስ፣ ባትሪ እና የስለት መሳሪያዎች እንደተገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተጠርጣሪው ወጣት ሰውነቱ በመጎዳቱና አቅም በማጣቱ፣ ራስ ደስታ ሆስፒታል ገብቶ ለአምስት ቀናት የህክምና እርዳታ የተደረገለት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአራዳ ክ/ከተማ ፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ ጠቁሟል፡፡ ፒያሳ የሚገኙ አብዛኞቹ ወርቅ ቤቶች በመደብራቸው ውስጥ እያንዳንዳቸው ከ2 ሚ.ብር ያላነሰ የወርቅና ብር ጌጣጌጦች እንዳላቸው ምንጮች ሲገልፁ፤ በዚህ ዓመት ብቻ በእነዚህ ወርቅ ቤቶች ከአራት ጊዜ በላይ የዝርፊያ ሙከራ እንደተፈፀመባቸው ፖሊስ ገልጿል፡፡

addis admas

“የፕረስ ነጻነት በዴሞክራቲክ ልማታዊ መንግስት ድባብ ውስጥ”

“የዴሞክራሲዊ ልማታዊ መንግስትና መገናኛ ብዙሃን ግንኙነት (nexus)” በሚል ርዕስ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው ሲምፕዚየም ላይ የቀረበ መነሻ ጽሑፍ
ሙሼ ሰሙ
ከመርህ አኳያ ማንኛውም መንግስት የኢኮኖሚ ስርዓቱ ልማታዊም ሆነ ሊብራሊዝም ፋይዳው የሰውን ልጅን ቁሳዊና መንፈሳዊ ልማት ማረጋገጥ ነው፡፡ እንደ ፋሺዝም ካሉ ለሰው ልጅ ጠር ከሆኑ የፖለቲካ ፍልስፍናዎች በስተቀር የመንግስታት ርዕዮተዓለም ከየትኛውም የፍልስፍና ማዕከል ቢነሳም ዴሞክራሲያቸው በይዘትም ሆነ በቅርጽ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን እስካልቻለ ድረስ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴትን ለሕዝብ ማድረስ አይቻለውም፡፡ እያንዳንዱ ስርዓት በቅርጽና በይዘት ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለመገኝት መሰረታዊ መገለጫው የሆኑት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነጻነት፣ የስልጣን ክፍፍል (Separation of power) የመሳሰሉ እሴቶቹ ተግባር ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሚንጸባረቅባቸው መሰረታዊ መገለጫዎቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ የሳንሱር ስለት የማይጎበኛቸው፣ መረጃ ያልተራቡ፣ የማይዋከቡ ነጻ ፕሬስና የሕትመት ውጤቶች መኖራቸው ነው፡፡
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሳንሱር ስለት ተነስቶለት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ውስጥ ተካቶ ጥበቃ ካገኘ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ መሰረታዊ የሕገ-መንግስታችን አንቀጾቹ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመነጩ ቢሆኑም በሕገ-መንግስታችን ላይ የሰፈሩት የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች የተወሰዱት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታህሳስ 10 ቀን 1948 ዓ.ም ካጸደቀው የሰብአዊ መብቶች ኮንቬንሽን ላይ ሙሉ በሙሉ በመሆኑ የሚወክሉት ሊብራል ዴሞክራሲን እንጂ ሌላ የፖለቲካ ስርዓት አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ከመቀበል አኳያ ሕገ-መንግስቱ በተሻለ መሰረት ላይ የተገመደ በመሆኑ የፕረስን ነጻነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ የተሻገረ ሆኖ አገኝቼዋለሁ፡፡ ይልቁንም ጥያቄ የሚሆነው የፕረስ ነጻነት ምን ያህል ወደ ታች ወርዶ ተግባራዊ መሆን ችሏል? ይህንን መብታችንን ከሚጨፈልቁና ከሚያቀጭጩ መንግስታዊም ሆነ ድርጅታዊ ወይም መዋቅራዊና ተቋማዊ መሰናክሎች ምን ያህል ጥበቃና ከለላ አግኝቷል የሚለው ነው፡፡
ርዕሳችን “Freedom of the Press in the Environment of Democratic Development State” የሚል ነው፡፡ አባል የሆንኩበት ፓርቲ (ኢዴፓ) የሚከተለው የፕሮግረሲቭ ዴሞክራሲያዊ ሊብራል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና ከልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብም የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡
ልማታዊ መንግስት በባሕርይው የዴሞክራሲ ሻምፒየን ነን ከሚሉት ከኒዎ ሊብራሊስቶች ጋር የሚያስተሳስረው ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ስላለበት የነሱን ይሁንታ ለማግኝት ሲባል በስም ሃሳብን የመግለጽ መብትን የማይከለክል ሲሆን
በተግባር ግን እንደ ጸረ-ሽብር ሕግ ያሉ ፖለቲካዊና መረጃን በተለያየ መንገድ የሚነፍጉ አስተዳደራዊ መንገዶችን በመከተል ሃሳብን በነጻነት መግለጽን የሚደፈጥጥ ነው፡፡ እቅዱ እንደ አስፈላጊነቱም ሶሻሊስቶች ኪነት ለመደቧ ትቆማለች በሚሉት መንገድ ለነጻ ፕረሱ አባላት በጅምላ ልማታዊ ጋዜጠኛ የሚል ተቀጥላ በመስጠት የልዩነት ኃሳብ ያላቸውን ከልማት ጋር የሚቃረኑ በማስመሰል ከሕዝብ ተነጥለው እንዲታዩ በማድረግ፣ በስጋት ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ሳንሱር የሚያደርግ ጋዜጠኞችን መፍጠር ነው፡፡ በተለይ ግን የልማታዊ መንግስት አስተሳስብ ለፕረስ ነጻነት ፈታኝ ከሚባሉት የፖለቲካ ስርዓቶች ባልተናነሰ መልኩ ለመታገልና ለማረም እንዳይቻላቸው መንገዱን በሙሉ ያጠረና እራሱን ያመቻቸ ስርዓት ነው፡፡
ዩ ኤን ዲ ፒ 2012 ላይ ባወጣው Democratization in a Developmental State: The Case of Ethiopian Issues, Challenges, and Prospects በሚለው የሕትመት ውጤቱ ገጽ 3 ላይ አንዳስቀመጠው ልማታዊ መንግስት ከኢስት ኤዢያ ሃገራት አኳያ ሲታይ ቀጥተኛ ትርጉሙ በመንግስት የሚመራ የኢኮኖሚ ስርዓት ማለት ነው፡፡ መንግስት ኢኮኖሚውን እንዲመራ ለማድረግ ከግብር የሚሰብሰብው ሃብት ብቻ በቂ ልማት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ልማትን ለማምጣት በግል ባለሃብትም ሆነ በጋራ የተያዙ እንደመሬት ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶቻችን ጨምሮ በማንኛውም የግልና የጋራ ንብረቶችና ሃብቶች ላይ በፖለቲካዊና በአስተዳደራዊ ውሳኔ በትዕዛዙ ስር እንዲወድቁ ማድረግን አለበት፡፡ የዜጎችን ገቢ በመዋጮ ስም በማሰብሰብና ዝቅተኛ ደሞዝን በመክፈል ፍጆታን(Consumption) በመቀነስ፤ እንደ ቦንድ ግዢ ያሉ ሃብት ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመዘርጋት አስገዳጅ (Forced) የሃብት ክምችትን መፍጠር ይኖርበታል፡፡ ግዙፍ መንግስት ለመሆን በሃብታቸው ላይ ማዘዝ የማይችሉ ጉርድ ዜጎችን መፍጠር አለበት፡፡ በአሰገዳጅ ሁኔታ የተሰበሰበውን ሃብትም የነጻ ገበያ ስርዓትና ውድድር ከሚፈቅደው ውጭ ቤተ መንግስት ውስጥ ቁጭ ብሎ ለማዘዝ የሚችለው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መጻረር ሲችል ብቻ ነው፡፡
መንግስት ባህርይው ሲገለጽ ለብክነት፣ ለዝርክርክነትና ለሙስ የተጋለጠ ቢሮክራቲክ ተቋም ነው፡፡ መንግስት በገዘፈ ቁጥር ለክትትልና ለቁጥጥር የማይመች ከመሆኑም በላይ አባካኝነቱና ለሙስና ተጋላጭነቱ በእጅጉ ይጨምራል፡፡ ግዙፍ በሆነ ሃገራዊ ሃብት ለማዘዝ የሚፈልግ መንግስት የዋች ዶግ ሚና ያላቸው ነጻና ሚዛናዊ ኢንቨስትጌቲቭ ጋዜጠኞች እንዲኖሩ አይሻም፡፡ ልማታዊ መንግስት ልማታዊነቱ በርብርብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አወቃቀሩ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መንፈስን ጨምሮ የላቀ የአሰራር ስልትና የቁጠባ ስርዓት እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ልማታዊ መንግስታት በአስገዳጅ ሁኔታ(Forced accumulation) አማካኝነት የሚሰበስበው ሃብት ግዙፍ ነው፡፡ ይህንን ግዙፍ ሃብትና ልማታዊ እንቅስቃሴውን የሚመራና የሚስተባበር ደ ውጤት የሚያደርስ አስተማማኝ መዋቅር በደሞዝተኛ አቅም ማስተዳደር የማይቻለው በመሆኑ ሃገራዊ ሃብቱ ለሙስና ለብክነት፣ ለዝርክርክነትና ለወገንተኝነት መጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሙስና፣ ብክነትና ዝርክርክነት የስርዓቱ መገለጫነታቸውን ተቀብሎና በገሃድ እወቅና ሰጥቶ በሚተርፈው ሃብት ልማትን እየገነቡ ተደግግፈው የሚኖሩ ናቸው፡፡
ልማታዊ መንግስት በዚህ መልኩ ለሙስና፣ ለብክነትና ለዝርክርክነት እንደሚጋለጥ አምኖ ተደጋግፎና ተቻችሎ ለመኖር በርካታ ከለላዎችና ሽፋኖች ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህ ሽፋኖቹንና ከለላዎች ሊፈጥር የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ባሕርይውን በማጣት ብቻ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ ኖረውም አልኖረውም ይህንን ምሽግ አልፈው ሊመጡ ከሚችሉት ገለልተኛ አካላት መካከል የመጀመርያ ሰለባ የሚሆነው ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ነው፡፡ የፕሬስ ነጻነት የሚሻውን
ተገቢውን ጥበቃ፣ እገዛና ከለላ በአስተዳደራዊና በፖለቲካዊ መንገድ በመሸርሸር ደካማ ያደርጋል፡፡ የሚፈለገውም የመረጃ ጥማት ያለበት፣ በአስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ወከባ ውስጥ የሚናጥ ፕሮፊሽናሊዝምም ሆነ ገለልተኝነትና ሚዛናዊነት የጎደለው ፕረስ መፍጠር ነው፡፡ ልማታዊው መንግስት ነጻ ፕረሱን አለ ወይም የለም ለማለት በማያስደፍር መልኩ በስጋትና በጥያቄ ውስጥ አንጠልጥሎ የሚያስቀርው ስርዓት ነው፡፡
ልማታዊ መንግስትና ነጻው ፕረስ ያላቸው ተቃርኖ ከነመሰረታዊ መገለጫቻው ጋር በጥቅል ለማገናዘብ የሞከርኩበት መነሻ ምክንያት የልማታዊነት አስተሳሰብ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ቅድሚያ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ተቀምሮለት እውን የሆነ ባለመሆኑ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት (Empirically) የተተነተነ በመሆኑ እንደየሃገሩ ተጨበጭ ሁኔታ ፈረጅ ብዙ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትንታኔዎች የሚለዩባቸው ነጥቦች ስስ ቢመስሉም አንዱን በሌላው ማዕቀፍ ውስጥ ማይት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ ብዙም አይዘልም፡፡ ልማታዊ መንግስታት በፕረስ ነጻነት ላይ ያለቸውን ተጽእኖ ስናጤነው በሁሉም ውስጥ የሚንጸባረቅ አንድ መሰረታዊ አንድነት አለ፡፡ ይህውም ድሕነትን ለማጥፋትና ከበለጸጉት ሃገሮች ተርታ ለማሰለፍ በሚል ከለላ የሚደረገውን ትግል ማጽድቅ አድርገው ስለሚወስዱት ነው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ዓይነቱ ትግል ጋር በተጻራሪ የሚቆም ማንኛውም የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደ መብት እውቅና ቢያገኘም በመርህ ደረጃ እንደ አፍራሽና ጎታች ስለሚፈረጅ ለአስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ጥቃት የሚያጋልጥ ነው፡፡
የኢህአዴግን ልማታዊ መንግስት ሃሳብን ነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር ያለውን ተቃርኖ በሁለት መንገድ አቀርባለሁ፡፡ የመጀመርያው ልማታዊ መንግስት ነኝ ሚለው ኢህአዴግ ቁሳዊ ፍላጎትንና መንፈሳዊ ልዕልናን (ዳቦና መብትን ማለት ነው) በማወዳደር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ሚዛን ላይ የሚያስቀምጥበት መስፈርት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከመዋቅራዊ (Structuralist) ወይም ከተቋማዊ (Institutionalist) ልማታዊ መንግስት ይዘትና ባሕርይ ወይም መገለጫዎች አኳያ ኢህአዴግ የሚከተለውን ስልት ይሆናል፡፡ መጀመርያ ግን ኢህአአዴግ ምን ዓይነት ልማታዊ መንግስት ነው?
ከላይ የተቀስኩት ዩ ኤን ዲ ፒ 2012 ላይ ያወጣው Democratization in a Developmental State: The Case of Ethiopia Issues, Challenges, and Prospects የሕትመት ውጤት ገጽ 4 ላይ ኢህአዴግ በ21 ዓመት የመንግስትነት ዘመኑ በተለያየ ጊዜ ተግባራዊ ካደረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች አኳያ ሲመዘን ልማታዊ ነው ለማለት እንደሚያዳግት ያትታል፡፡ ኢህአዴግ የመንግሰታዊ ተቆጣጣሪነት( Regulatory state) ሚና ሲጫወት አይተናል፡፡ በተለያዩ ቁሳቁሶችና ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን በመጣል የተጠናወተው ሶሻሊስት ዝንባሌውን አሳይቷል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የዊልፌር ስተቴ ሚና( Welfare State) ሲኖረው ተመልክተናል፡፡ ያለ አንዳች እርሾና ቁጠባ መነሻ በአነስተኛና ጥቃቅን ስም የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ገንዘብ አድሏል፡፡ አሁንም የጣልቃ ገብነት( Interventionsit states )ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የግል ባንኮች ካሰባሰቡት ተቀማጭ ውስጥ 27 ፐርሰንቱን የአባይን ግድብ ቦንድ በዝቅተኛ ወለድ እንዲገዙ አድርጎል፡፡ ዜጎች ለዘመናት በመኖርና በማልማት የግላቸው ያደረጉትን የመሬት ባለቤትነት ትርጉም አሳጥቷል፡፡
በልማታዊ ስርዓት ላይ ሰፊ ምርምር ያደረጉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የዲቭሎፕመንታል ስቴት ፍልስፍቸውን አስመልክቶ ALEX DE WAAL THE THEORY AND PRACTICE OF MELES ZENAWI በሚለው ሪቪዋቸው ላይ የአቶ መለስን “African Development: Dead Ends and New Beginnings’, እና State and markets: neoliberal limitations and the case for a developmental state” የተሰኙ ጽሁፋቸውን በመጥቀስ
እንዳቀረበው አቶ መለስ የልማታዊ መንግስት መነሻቸው ከድህነት በላይ ጠላት የለንም የሚልን መርህን ያነገበ ነው፡፡ ቅድሚያ ለየቱ መስጠት ይኖርብናል የሚል ነው፡፡ ለዳቦ ወይስ የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫዎቻችን ለሆኑት ለዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቻችን፡፡
አንዱ በአንዱ ውስጥ ስለሚገኙም በዚሁ ሪቪው ላይ አቶ መለስ ድህነትን ለመታገል ብቸኛው አማራጭ ዴሞክራቲክ ልማታዊ መንግስት እንደሆነም ይተነትናሉ፡፡ ሆኖም ግን ይላሉ “የሊብራል ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶችምና የዴሞክራሲያ ጥያቄዎች (የፕረሱ ነጻነት) ጨምሮ ስር የሰደደ ድህነትና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ባለበት ሁኔታ ትርጉም እንደሌላቸው ያሳስባሉ፡፡” ይህ ማለት ደግሞ ድሕነትን ሳያጠፉ ስለ መብት ማሰብ ከንቱ ነው ወደሚል ድምዳሜ ሊደርሰን የሚችል ጎዳና አለው፡፡
አሌክስ ዲ ዋል እንዳስቀመጠውም ቁሳዊ ጥቅም በመንፈሳዊ ልዕልና (ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች) ለመተካት መፈለግ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጀምሮ በዜጎች ላይ የሚኖረውን አጠቃላይ ተጸእኖና እንደምታ በጥሞና መመርመር አስፈላጊ ነው በሚለው ሃሳብ ላይ እስማማለሁ፡፡ የሰው ልጅ ሙሉ ካደረጉት መሰረታዊ መብቶች መካከል ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ የሰው ልጅ እነዚህንና መሰል መሰረታዊ መብቶቹን የዕለት ተእለት ፍጆታውን ለማሸነፍ ሲባል ብቻ ለአምባገነኖችም ሆነ ለልማታዊ መንግስታት አሳልፎ እንደማይሰጥ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በመርህ ደረጃም ቢሆን በሚል በሁለቱ መካከል “ቀይ መስመር ” ማስመር የማይቻል (dichotomy) ነው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ሊሟሉም ሆነ ሊረጋገጡ አይችሉም፡፡
በአቶ መለስ ዜናዊ ትንታኔ መሰረት ልማታዊ መንግስታት ዓይነታቸው በርካታ ነው፡፡ እንደ ኢስት ኤዢያ ሃገራት ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሊሆኑ ይችላሉ ወይም እንዳሳቸው ፍላጎት በአንድ ላይ “ዴሞክራሲያዊ” ና “ልማታዊ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ኢህአዴግ ልማታዊነት መሆን መርሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ዴሞክራቲክ መሆኑ ግን ቀቢጸ ተስፍ ብቻ ነው፡፡ መግባባት የሚያዳግተንም እዚሁ ልማታዊነትና ዴሞክራሲያዊነቱ ላይ ነው፡፡ ወደ አቶ መለስ ትንታኔ ስንመለስ “የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት ለመፍጠር ከተፈለገ ሌላ ተጨማሪ ሶስተኛ እሴት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ ፡፡ እሴት ሌላ ሳይሆን “የዲቭሎፕመታል ዲስኮርስ ሔጅመኒን ማረጋገጥ ነው፡፡” ስለ ሔጅመኒ ስንናገር በእርግጠኝነት እየተናገርን ያለነው ስለ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም አቶ መለስ ሊከተሉት የፈለጉት ዴሞክራሲ እንደ ዴሞክራቲክ ስልት ከወሰድነው ዴሞክራሲያቸው አማራጭ የሌለበት “ዲሞክራሲ” (No Alternative Democracy) ነው፡፡ ዴሞክራሲያቸው የሚያወሳው ስለነጻው ፕረስ መጠናከር ወይም ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ አይደለም፡፡ ይልቁንም በታቀደለት ትልም ውስጥ ተከቦ ስለልማት እየዘመረ የሚተም ልማታዊ ሕዝብ፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ልማታዊ አርቲስት፣ ልማታዊ የሃይማኖት መሪ ወዘተርፈን …. ስለ መፍጠር ነው፡፡
ኢህአዴግን ከመዋቅራዊ (Structural) አስተሳስብ አኳያ ምን በምን አንደሚገለጽ እንመልከተው፡፡
በልማታዊ መንግስት ላይ የተለያዩ ትንታኔ የሰጡ ምሁራን መካከል ቻልመርስ ጆሰንና Developmental State Odayssey of a Concept እና Ziya Onis the Logic of The Devlopmental State በሚሉት የተለያዩ መጻሓፎቻቸው ላይ
ልማታዊ መንግስት ከመዋቅራዊነት (Structuralist) ዝንባሌ አኳያ ያስቀመጡበት መንገድ የኢህአዴግን ልማታዊ መንግስትነት በቅጡ የሚገልጽ ነው፡፡
እንደ ኢስት ኤዢያ ያሉትን ልማታዊ መንግስታት መዋቅራዊ ሽግግርን ማዕከል ያደረጉ ሲሆኑ ፡፡ እንደ ላቲን አሜሪካ ያሉ ልማታዊ መንግስታት ግን ተቋማዊነትን ማዕከል ያደረጉ እንደሆኑ ይገልጾቸዋል፡፡
መዋቅራዊ ሽግግርን ማዕከል አደርገው፤ ልማታዊ የሆኑ መንግስታት የመዋቅር ሽግግርን እውን ለማድረግ ሲሉ ኢህአዴግ ደጋግሞ እንደሚገልጸው ለ40 እና 50 ዓመታት በስልጣን ላይ መቆየት አማራጭ የሌለው መብት ነው፡፡ እነዚህ ልማታዊ መንግስታት ለዚህ ሲባል ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ ውሳኔ ከመወስን የማይመለሱ ናቸው፡፡ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጨምሮ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን እስከማፈንና ምርጫን እስከ ማጭበርበር ድረስ የሚዘልቁ ናቸው፡፡
ሌላው መገለጫቸው ሰፊ ሃብትና ግዙፍ መንግስት ለልማትዊ እንቅስቃሴያቸው አስፈላጊ በመሆኑ ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት የግድ ይላቸዋል፡፡ እንደ ኮርያ ያሉት ሃገራት የቻይና ኮሙኒዝም ጥላውን አጥልቶባቸው ስለነበርና በብሄር ደረጃም የአንድ ብሔር አባል በመሆናቸው ብሔራዊ መግባባትን ፈጠሮ ሃገራዊ መነቃቃትን ለማስፈን ችግር አልነበረባቸውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ግን ብሔራዊ አንድታችንና ብሔራዊ መግባባታችን በልዩነታችንና በተጽእኖ የተዳከመና የተሸረሸረ በመሆኑ ምክንያት ብሔራዊ መግባባትንም ሆነ መነቃቃትን በቀላሉ ለማስፈን እንኳን ለኢህአዴግ ለማንም አዳጋች ነው፡፡ ሃብትን በሕዝብ ይሁንታ በማከማቸት በሕዝብ ውሳኔ ለልማት ለማዋል በብሔራዊ መግባባት ውስጥ ብሔራዊ መነቃቃትን መፍጠር ለማንኛውም መንግስት እጅግ አስፈላጊ እሴት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አስፈላጊ እሴት ከሌለ ወይም እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከተሸረሸረ ሃብትን በተጽእኖና በአስገዳጅ ሁኔታ ማከማቸቱ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ እነዚህ እሴትቶች በጉደሉበት ሃገራት ልማታዊ መንግስት ለመሆን የሚቻለው የተቃውሞ፣ የልዩነት ድምፅን በማፈንና እጅግ አስገዳጅነት በተቀላቀለበት መልኩ ይሆናል፡፡
ሌላው የራዕይ ጉዳይ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ተቋማዊ (Institutional) ልማታዊ መንግስታት ቢያንስ ራዕያቸው በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ አውቶኖሚን ለቢሮክራሲው በመስጠትና የግሉ ዘርፉ እና የሕዝብን ትብብር በማቀናጀት ራዕይ ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ መቀናጆ ውስጥ የሚወለድ “ራዕይ” ደግሞ የሕዝብ ቀጥተኛ ነጸብራቅ ስለሆነ መንግስት ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡ መዋቅራዊ ለሆኑ ልማታዊ መንግስታት “ራዕይ” ማለት ደግሞ በጠባቡ ዓለማቸው ውስጥ ከአስፈጻሚዎቻችው ጋር የሚቀምሩት “እውቀት” ነው፡፡ ራዕያቸው ሕዝብ የሚፈልገውንና ከነባራዊ ሁኔታው የሚወለደውን ሳይሆን በጠባብ መድረክ በጥናት ደረስንበት የሚሉትን ነው፡፡ ሕዝቡንም የሚፈልጉት ለተግባራዊነቱና ለአስፈጻሚነቱ ነው፡፡ መዋቅራዊ (Structural) ልማታዊ መንግስታት ከራዕይ አለመጣጣም (Incompatable Vision) የተነሳ በሕዝብና መንግስት መካከል ራዕይ ልጋትህ አልጋትም ትንንቅ መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መሃል ልዩነትን ለማደብዘዝና የዜጎች ይሁንታ ባይኖረውም የዓላማና የግብ አንድነትን ለመፍጥር በሌላ በኩል ደግሞ ልዩነትንና ሃብን ለማዳከም በአጠቃላ መረጃን ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ መሰወር ወይም አደናጋሪ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይህንን ጊዜ እንደሌሎቹ መብቶች ሁላ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የመጀመርያው ሰለባ ይሆናል፡፡
ሌላው መዋቅራዊ (Structurual) ልማታዊ መንግስት ጠንካራ በሆነ ተቋማዊ (Institutional) አቅም ላይ ሳይሆን በፓርቲና በግለሰብ ዲሲፕሊን ላይ ስለሚያተኩር ለሕዝብ ጆሮና ዓይን መድረስ የሚገባቸውን መረጃዎች ለመሰወርና ለማድበስበስ የተመቻቹ ናቸው፡፡ መዋቅራዊ ልማታዊ መንግስታት ድርጅታዊም ሆነ መንግስታዊ ሙስና፣ ብክንትና ዝርክርክነት የስርዓቱ አማረጭ የሌለው ደካም ጎኑ እንደሆነ ይቀበላሉ፡፡ ነገር ግን አጥፊውን ለሕዝብ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኝነትም ሆነ ቁርጠኝነት የላቸውም፡፡ ይልቁንም አጥፊዎቹን ከመቅጣ ይልቅ በድርጅታዊ ግምገማ አማካኝነት ለልማታዊ ስርዓቱ ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ በመሃላና እያረጋገጡ ከጥፋታቸው ሳይማሩ በጥገናዊ ለውጥ ወይም ባሉበት እንዲቀጥል በር የሚከፍት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ምርመራዊ ጋዜጠኝነት እና አማራጭ ሃሳብ የሚያመነጭ ነጻ ፕረስ (Investigative Journalism) አይፈልጉም፡፡
6ኛ ዓመት፣ ቅፅ 3፣ ቁጥር 1፣ 2006 ዓ.ም የታተመው የብአዴን ድርጅታዊ ልሳን የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔት ስለ መዋቅራዊ ልማታዊ መንግስት ራዕይን አስመልክቶ እና ሙስናንና ዝርክርክነትን በዲስፕሊን ስለማረቅ ሲጠቅስ “የልማታዊ መንግስታት አስተሳሰብን ውጤታማ ለማድረግ ጥብቅ ዲስፕሊን ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መንግስታቱ መላ ህዝቡን የሚያነቃንቅ ራዕይ ይነድፋሉ። ራዕያቸውን የሚያሳኩ ግቦችን ቆጥረው ያስቀምጣሉ” ይላል
ልማታዊ መንግስት ከፕረስ ነጻነት ጋር ያለው ተቃርኖ ለመረዳት ከላይ የቀረቡት ምሳሌዎች በርካታ አመላካች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእኔ እምነት ግን ኢህአዴግ ከልማታዊ መንግስትነቱ ይልቅ እራሱን የሚያይበት መነጽር በፕረስ ነጻነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከሁሉም የገዘፈው ችግር ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ እራሱን የሚያይበት መነጽር እጅግ የተዛባ ነው፡፡ ፓርቲው ራሱን የሚስለው በዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ውስጥ እንደተፈጠረ አንድ ተወናይ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመታደግ አንዳች ተልዕኮ እንዳለው ኃይል አድርጎ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልሙ እስኪሰምር ድረስ አማራጭ በቅጡ የማይታይበትና የማይደመጥበት ድባብ ፈጥሮ፤ ዜጎች የሚከፈለው ሁሉ መስዋእትነት እየከፈሉ እስከ ዘንተ ዓለሙም ቢሆን በስልጣን ላይ መቆየት እንዳለበት ያምናል፡፡ ይህንንም አበክሮ እየሰበከ ይገኛል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሁሌ በኩሉ (Omnipotent) ተልዕኮ ያነገበ ሃይል ደግሞ ሁሉን አቀፍ፣ የማይሳሳት፣ ፍትሐዊና ርትዕዊ ነኝ ለሚለው እምነቱ ሲባል ማንንም አማራጭ ሃይል በፖለቲካዊና በአስተዳደራዊ መንገድ ለማንበርከክና ደንቃራ የሚለውን ሃይል ስልታዊ ( systemic) በሆነ መንገድ ለመጨፍለቅ የሚያግዘውን ስውር የሆነና የተቀነባበረ ስልት ቀምሮ በውስጡ አምቆ የሚይዝ ስርዓት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚቃኙ ፓርቲዎች ተልዕኮቸውን ለማሳካት በገለልተኛ አካል የማይፈተሹና በከፍተኛ ደረጃ ሚስጥራዊ ከመሆናቸውም በላይ መብቶችና ሕግጋትን ለዓላማቸው ተገዢ (Subserviant) የሚያደርጉ ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ ልዩ ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎቹ ከድርጅታዊ ድባብ ወጥተው መንግስት ከሆኑም በኃላ ቢሆን መለኪያን መስፈርት በሌለው (Interparty) ውስጠ-ድርጅትዊ የነበረውን ጥብቅና ሚስጥራዊ አሰራር ወደ መንግስት መዋቅር በማምጣት በሃሳብም ሆነ በልዩነት የሚታገሏቸውን ከማዳከምና ከማጥፋት የማይቦዝኑ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በመንስኤ፣ ክንውንና ተገብሮት (Cause, process and Effect/Consequence) የማይመሩ ነገር ግን ሁለንተናዊ ፍትሕና ርትዕን ለማስፈንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በእኩልነት ለማደላደል ልዩ ተልዕኮ ያነገበን ነን ብለው የሚያምኑ ሃይሎች
ነጻነትንና መንፈሳዊ ልዕልና ላይ ምን ያህል ፈተና ሊደቅኑባቸውና ዋጋ ሊያስከፍሏቸው እንደሚችሉ ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም፡፡
ነጻው ፕሬስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ታሪክ በጣም አጭር ነው፡፡ በደርግ ስርዓት ዋዜማ ላይ ብልጭ ብሎ ከመጥፋቱ በስተቀር ለበርካታ ዓመታት የሚነገርለት ታሪክ አልነበረውም፡፡ ካለውም በተናጠል የነጻ ፕረሱ አባላት ወይም ሌሎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር የተካሂደው ተጋዶሎ ውጤት የሚንጸባረቀው ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የፕረስ ነጻነት በሕገ-መንግስቱ ላይ ሰፍሮ ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ እንዲያገኝ ብዙ መስዋእትነት የተከፈለለለት መብት መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
በተለይ ደግሞ 1983 ዓ.ም ላይ የነጻው ፕረስ ውጤት ከሌሎቹ መብቶች ሁሉ ቀድሞ ሕገ መንግስት ላይ ሳይሰፍንና ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖር ሕልውናው እውን በመሆኑ ብቻ ከፍተኛውን ዋጋ ከፍሏል፡፡ ነጻ ፕረሱን የተወዳጁትም ሃቀኛ የነጻ ፕረሱ ባለቤቶቹ ሳይሆኑ ቅድመ ዝግጅት የነበራቸው የደርግ ባለሟሎች ነበሩ፡፡ በዚህ መልኩ ነጻ ፕረሱን የተቆጣጠሩት የደርግ ባለሟሎች በጦርነት ከተሸነፉም በኃላ ቢሆን ከሕዝቡ አልፎ እራሳቸውን ባደነቆራቸው ፕሮፓጋናዳ ምክንያት ሽንፈታቸው ያለየለት ይመስላቸው ስለነበር፤ ነጻ ፕረሱን እንደ አዲስ የትግል መሳርያና ስልት በመውሰድ የፕረሱን ሚና ከኢህአዴግ ጋር መናቆርያ ብቻ አድርገውት ነበር፡፡
በተለይ ደግሞ ማርክስ በ8th ብሩሚየር ላይ “በጦርነቱ የተሸነፉ በሊትሬቸር ይመጣሉ፡፡” እንዳለው በፕረሱ ነጻነት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱትና በጦርነት የቆሰለ ሽንፈታቸውን ማጠብያ ያደረጉት የደርግ ባለሟሎች ፕረሱ የተቀዳጀውን ነጻነትና ሚና በመርሳት እርስ በርስ መራኮቻ በማድረጋቸው ምክንያት የነጻ ፕሬሱ ሚና ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የሚንሸራሸሩበት መብቶቻችውን ለማስከበር የሚታገሉበትና መረጃ የሚቋደሱበት መድረክ ሳይሆን ደርግና ኢህአዴግ ያልተቋጨ “የሚመስለውን” ቀጣይ ፍልሚያ “በአፍ-እልፊ” የሚፋለሙበት ነበር፡፡
ዛሬም መንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌላው የማህበረሰብ አካላትና የሙያ ማህበራት አቅፈውና ደግፈው በባለቤትነት መንፈስ እንዲራመድ በቂ እገዛ እያደረጉለት አይደለም፡፡ እርስ በርሱም ሆነ ከስርዓቱና ከመንግስት ጋር እየታገለና እየተራረመ በሂደት ተጠናክሮ እንዲወጣ አንዳችም የተመቻቸ ሁኔታ የለም፡፡ ነጻ ፕረሱ በራሱ እግር የቆመ ጊዜ ቢያንስ ጠቃሚነቱ ለኔ ነው በሚል መንፈስ ጋዜጣዎቹንና የሕትመት ውጤቶቹን በማንበብና አቅጣጫ በማስያዝ እያገዘ አይደለም፡፡ በዚሁ ምክንያት ሽያጩም ቢሆን በቂና የሚያወላዳ ካለመሆኑ የተነሳ ነጻ ፕረሱ በቂና ፕሮፌሽናል የሰው ኃይል ቀጥሮ ማሰራት አልቻለም፡፡ ከዚህም በላይ ነጻ ፕረሱ መረጃ ለማግኝት የሚያስፈልገውን ቁሳዊና ሰብአዊ ዋጋ ከፍሎ መረጃን ለማገኘት የሚያግዘውን በቂ አቅምም ፈጥሮ አያውቅም፡፡ በድንገት ከሕገ መንግስቱ በፊት ነጻ በመሆኑ የራሱ ባለቤትን በመፍጠርም በኩል በቂ ስራ አልተሰራም፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ቢሆን የነጻ ፕረሱ ምሰሶ የሆኑት ፕሮፊሽናሊዝምንና ገለልተኛነትነ በበቂ መጠን ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ ከዚህም ለመረዳት የሚቻለው ነጻ ፕረሱ በተናጠል በሕትመት ሚዲያ ውስጥ የሚገኙ ዋነኛ ተጠሪ አባላቱ ከሚከፍሉት እጅግ መራራ መስዋእትነት በስተቀር ቋሚ የሆነ የትግሉ አጋዢ ሃይሎችን ለማበጀት አለመቻሉን ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው መንግስት የነጻው ፕረስ ባለቤት እስኪረጋገጥ ድረስ አግባብ ያለው ጥበቃና እገዛ ለማድረግ አለመሞከሩና ፍላጎት ማጣቱ ነው፡፡ ለዚህም መነሻ ምክንያቱ ገዢው ፓርቲ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በራሱ አምሳይ እንደቃኘው ሁላ ነጻ ፕረሱንም በዚሁ መንገድ ለመቃኘት መሞከሩ በመካከላቸው ከፍተኛ አለመተማመንን መፍጠሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ነጻ ፕረሱን በሕዝብ ጠላትነት ከመፈረጅ ጀምሮ የተለያየ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥቃት እንዲያደርስበት ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በተነጻጻሪ ስንመለከተው አለመተማመኑ ስር እንዲሰድ አንዳንድ ጽንፈኛ ሃይሎች ሚና ቢኖራቸውም ነጻ ፕረሱ እራሱን ከመንግስት ለመከላከል ሲል ከመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን የሚወጡ መረጃዎችን እንደ ፕሮፓጋንዳ በመቁጠር ተጻራሪ የአጸፋ መልስ ለመስራት እንዲገደድ ሆኖል፡፡
ሁለተኛው መንስኤው ከዚህ ፍረጃ በመነጨ ምክንያት ነጻ ፕረሱ በቂ መረጃ ለማግኘት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለት ከፍተኛ አደጋዎች እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ አንደኛው አደጋ ጋዜጠኞች መረጃን ፍለጋ እጅግ አደገኛና ከባድ ውጣ ውረድና መስዋእትነትን በሚጠይቅ ጥልፍልፍና ግብግብ ውስጥ እንዲገቡ መገደዳቸው ሲሆን ሌላ ደግሞ መረጃ የሕልውናቸው መሰረት እንደመሆኑ መጠን ሕልውናቸው እንዳይከስም ሲባል መረጃን በጥሬው ወስዶ በማዛባትና አልፎ ተርፎም መረጃን በመፈብረክ ላይ እንዲሰማሩ መገደዳቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለመንግስት ቀጥተኛና ስውር ጥቃት አመቻችቷቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሶስተኛው በሃገራችን ውስጥ የውይይት (Discourse) ስርዓት አለመዳበሩና መድረኮች መጥፋታቸው ነው፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተለይ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ሲባል ብቻ የተቋቋሙ ይመስል በራቸው ክፍት የሚሆነው ለመንግስተና መንግስታዊ ተቋማት ደግፊ ነው፡፡ ዘገባቸውም ከዚሁ አጀንዳ አይዘልም፡፡ ይህ ደግሞ ከመንግስተ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ውጭ አማራጭ ሃሳብንና መረጃን የሚፈልግ ሕዝብ መረጃ ለመስጠት ከተቃዋሚው ሃይል ጋር የበለጠ የቅርብ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ የመንግስት መገኛኛ ብዘሃን መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ ሌት ከቀን የማቆለጳጰስ አባዜ በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ መሰላቸትንና የልዩነት ሃሳብን በጉጉት እንዲፈልጉ አድርጓል፡፡ ይህንን ሰፊ ገበያ ለመሸፈን ሲባል ደግሞ ነጻው ፕረስ ስሜትን ወደሚቀሰቅሱና ዓይንና ጆሮ ወደሚስቡ በተለይ ደግሞ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አስገድዷቸዋል፡፡
አራተኛው ደግሞ የንብብ ልማዳችንን ይመለከታል፡፡ በሃገራችን ውስጥ ያለው የንባብ ልምድ እጅግ በጣም ደካማ ለመሆኑ በአንድ በኩል ድህነታቸን የራሱን አሻራና ጠባሳ ጥሏል፡፡ እንደሚታወቀው ድህነታችን የጋዜጣና የሕትመት ውጤቶችን ሽያጭ ከገቢ አንጻር ከእጅ አይሻል ዶማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የጋዜጣን ስራ አትራፊና አዋጭ እንዳሆን አደርጓታል፡፡ በዚህም ምክንያት ቀላል ነጻ ፕረሱን ቀላል የማይባሉ አባለቱ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይልቅ በፖለቲካ እምታቸው ምክንያት እንዲቀላቀሉት አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ከፕሮፊሽናሊዝምና ከገለልተኛነትና ከሚዛናዊነት ይልቅ አቋም ወስደው የሚጽፉ የነጻ ፕረሱ አባላት ቁጥር ከፍተኛ አድርጎታል፡፡
በተለይ ደግሞ ከመንግስት በኩል የሚካሄደው ፋታ የሚነሳ ማዋከብ፣ ማሰርና ጫና አስጨናቂ በመሆኑ ምክንያት ወደ ነጻው ፕሬስ መፍሰስ የሚገባው የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመናመንና አስፈላጊው በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ፕሮፊሽናል
አጋዥ ሃይል እንዳኖረው ተገዶል፡፡ በዚህም ምክንያት በነጻው ፕረስ አባልነት የሚሰለፉት ጋዜጠኞችም ሆኑ ዘጋቢዎች ወይም አምደኞች በአብዛኞው ጫናውን ለመቋቋም የቆረጡ፣ ለእስርና ለእንግልት የተዘጋጁት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
ይህ ማለት ግን ነጻ ፕረስ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከጫናው በላይ አይደለም ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ነጻው ፕረስ የራሱ ሆኑ በርካታ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሴቶችን ፈጥሯል፡፡ ነጻው ፕሬስ ከሕግ አውጭው፣ ሕግ አስከባሪውና ሕግ አስፈጻሚው ባልተናነሰ መልኩ የገለልተኝነት ሚናውን በተለያየ ጊዜ ሲወጣ ቆይቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ነጻው ፕረሱ እንደ ሕዝብ የምንጠብቅበትን ሚና ተጫውቷል የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በርካታ መልስ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውና በርካታ ነጥቦችንም ማከል የሚቻል ቢሆንም፣ ለዚህ መድረክ ግን ይህ በበቂ ግንዛቤ የሚሰጥ ይመስለኛል ፡፡
ነጻው ፕሬስ በ1983 ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በደርግ ሹመኞችና በኢህአዴግ ሸኩቻ መሐል ተጠልፎ ከመቆየቱም በላይ ዛሬ ላይ አብዛኞዎቹ የቀደሞ አባላቱ አውላላ ሚዳ ላይ ጥለውት ሄደዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ነጻውን ፕረስ ሁለተኛው የፖለቲካ ትውልድ የራሱን ዜማና ቃና እየሰጠው ይገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ አመለካከቴ መሰረቱ በትውልድ ላይ ካለኝ እምነት የሚመነጭ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለነጻው ፕረስ በጎ ጊዜ መምጣት አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥም ዛሬ ላይ በርካታ ወጣቶች በከፍተኛ የጥንካሬ መንፈስ በነጻ ፕሬስ ውስጥ እየተሳተፉ፣ በባለቤትነትና በአንጻራዊ ሚዛናዊነት እየመሩት ይገኛሉ፡፡
በነጻው ፕረስ በኩል ያለው እውነታ ከሞላ ጎደል ይህንን ቢመስልም፤ አሳሳቢው ነገር ግን መንግስት ዛሬም ቢሆን በነጻ ፕረሱ ውስጥ በነበረው አንደኛ የፖለቲካ ትውልድ ምክንያት የተፈጠረውን የተዛባ እይታውን ማስተካከል አለመቻሉ ነው፡፡ በአብዛኘው በደርግ ፕሮፓጋንዲስቶች የተወረረውን የቀድሞ ነጻ ፕሬስ ከአዕምሮው ማውጣትም ሆነ መርሳት አለመቻሉና ወደ ሁለተኛው የፖለቲካ ተውልድ መሸጋገር አለመፍቀዱ ዛሬም ቢሆን ነጻ ፕረሱ ፕሮፊሽናሊዝም፣ ሚዛናዊነትና ገለልተኛነት የሰፈነበት ጠንካራ መረጃ መስጠት የሚችል የህዝብ አጋዥ ሃይል ለመሆን ብዙ አንዲቀረው ምክያት ሆኖል፡፡ በዚህም ምከንያት መንግስት እራሱን በቅጡ ሊመርምር የሚገባው ጊዜ ላይ ደርሷል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለማጠቃለል ያህል “ዴሞክራቲክ” ሆነ ልማታዊ መንግስት መገለጫዎቻቸው ለነጻ ፕረሱ ነጻነት ለመቆም እድል የሚሰጧቸው አይደሉም፡፡ ልማታዊ መንግስታት የኢኮኖሚ ስርዓታቸው መነሻ መሰረቱ የግለሰብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ሳይሆን አንድ ኢኮኖሚ መደብ እድገትና ብልጽግና ከመሆኑም በላይ ከዜጎችም መካከል በተለይ ቅድሚያ የሚሰጠውና ይበልጥ የሚቆረቆርለት ኃይል አለው፡፡ ለዚህ መደብና ዜጋም ሲባል ዜጎችን በእኩል ማየት የግድ የሚለውን የዴሞክራሲ ከባድ ዳገት መውጣት የሚቻለው አይደለም፡፡ ስለሆነም ልማታዊ መንግስት ፕረሱን የሚፈልገው በነጻነት እንዲንቀሳቀስና ዜጎች በአማረጭ እንዲወስኑ ሳይሆን የዳቦ ወይም ነጻነት ትግል አዝማሪ ማደረግ ነው፡፡ ልማታዊ ዲስኮርስና ሔጅመኒ ማለትም ይህው ነው፡፡ ለዜጎች መብትና ነጻነት ዘብ የሚቆምና በመረጃ የበለጸገ፣ ለመወሰን አማራጭ ያገኘና የቀረበለት ዜጋ መፍጠር ሳይሆን የመንግስትን ልዩ ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚተጋ እንደ ልማታዊ ባለሃብትና ሹመኞች ሁሉ ልማታዊ ጋዜጠኛ መፍጠር ነው፡፡