Archives

ይብላኝ ለወለደች

 images (3)

By Alemayehu Tibebu

 መአዛዋ ጠፍቶ በሃዘን ቆርቁዛ

አንገትዋንም ደፍታ በጣሙን ቀዝቅዛ:

ከመንገድ አግኝቼ ስምዋን ብጠይቃት

ሃገሬን አገኘሁ ሃገር እንደሌላት::

በይ ሂጅልን አልዋት ልብዋን አቆሽሸው

ጡትዎችዋንም ነክሰው ጨቅላ ልጅዋን ነጥቀው:

ባህር ይብላው አልዋት ስደት ያንከራተው::

ጀርባውም ይሸከም በርሃም ይምለጠው

እግራቸው ይመርቅዝ ይብዛ ስቃያቸው

ስንቱን ጀግና አባብሎ ካኖረው መዳፍሽ

ውሃ ጥም አቃጥሎ ጠኔ ይንገስብሽ?!

ጉልቻው ይቀየር ሌላውም ይተካ

ወጡ እንደው ላይጣፍጥ ጣ‘ሙ ላይቀይር

ከበሮው ይመታ ውዳሴ ይደርደር

ሃገር የለም ለኛ ከሆዳችን በቀር!

ብለው ፈረዱባት ሃገሬን እንደጠላት

ቦጥቡጠው መጠጥዋት:

ወዝዋንም በአመድ

ለውሰው ለውሰው ለውሰው

መቃብርዋን ምሰው!

ለስዋ ማንም የላት ካለኛ በስተቀር

ቢሻን በግልምጫ በጡጫ በርግጫ

ቀጥቅጠን ጠፍጥፈን

እንደፈለግን አርገን

እንገዛለን ገና……………ወንድስ የት አለና?

ብለው ዘበቱባት ሃገሬን በታትነው

ማንም እንደሌላት አይንን በጨው አጥበው::

 

እንደው ግን….

ጦሙንስ ጦማለች ……… እግዚኦ እያለች

ሶላትም ሰግዳለች ……… ዘካውን ሰታለች

ታድያስ ምን አጠፋች ምንስ አጐደለች?

እድሜ ልክ በስቃይ በፍዳ የኖረች?

ይች ሃገር የማን ናት?

በመንገድ የቆመች

በመከራ ወልዳ በ‘ራ የመገበች

በታንኴ ላይ ጭና ለ‘ዋ የገበረች!

አጥባና ገንዛ በቄስ አስፈትታ:

ካፈር ያልከተተች

ትናንትና ፈጥራ ዛሬን ያላኖረች::

እግዚኦ …… እግዚኦ………

እኔማ እኔ ነኝ

ይብላኝ ለወለደች::

 

በበርሃና በባህር ላለቁት

መስከረም 2006 ዓም

German