Archives

ዳያስፖራው በሁለት ቢሊዮን ብር ሆስፒታል ሊገነባ ነው

የኢትዮ-አሜሪካን ሐኪሞች ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ በሁለት ቢሊዮን ብር  ለሚያሠራው ሆስፒታል ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኖረ፡፡

ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው 30 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ በሚገነባውና በዓይነቱ ለኢትዮጵያ ልዩ በሆነው ሆስፒታል የአጥንት፣ የጅማት፣ የልብ፣ የደም ሥር፣ የጭንቅላትና ሌሎችም ቀዶ ሕክምናዎች የሚካሄዱበት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለዘላቂ የጤና አጠባበቅ ፕሮግራም የሚረዱ ተቋማትና ማዕከላት ይኖሩታል፡፡

ቡድኑ ሰኔ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የውስጥ ደዌ ሐኪምና የፕሮጀክቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ደምሴ  እንደገለጹት ከማዕከላቱም መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገሮች የሚገለገሉበት የካንሰር ማዕከል ይገኝበታል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ቡድኑ ከአባል አገሮቹ ጋር የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ሆስፒታሉ ዘመናዊ መመርመሪያ ቴክኖሎጂዎችና 300 አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ የኢትዮጵያንና አካባቢውን አገሮች ብሎም የአፍሪካን የጤና አገልግሎት ደረጃ ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይር የልቀት ማዕከል እንዲሆን የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሆቴል፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ቢሮዎች፣ የመድኃኒት መደብሮች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጂምና ወጌሻ እንደሚይዝ፣ አገልግሎት መስጠት በሚጀምርበትም ወቅት ለሕክምና ወደ ውጭ የሚሄዱትን ሕሙማን ቁጥር እንደሚቀንስ፣ ሜዲካል ቱሪዝምን ለመጀመር የሚረዱ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች፣ ለሕክምና ባለሙያዎችና ለሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ መስክ እንደሚፈጥርና ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ በሚገኙ 12 ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው ኢትዮ-አሜሪካን የሐኪሞች ቡድን በአሜሪካ እውቅና ያለው ሲሆን፣ ዓላማውም ኢትዮጵያ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሆስፒታል ማቋቋምና በጤናው ዘርፍ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡

ሆስፒታሉ እውን ሲሆን፣ በውጭ አገር ያሉ ከፍተኛ ትምህርትና ዕውቀት ያላቸው ሐኪሞች በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት ወደ አገር ውስጥ በመምጣት ያላቸውን ልምድና ዕውቀት የሚያካፍሉና የአገሪቱን የሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ለማጠናከር የሚሠሩ ይሆናል፡፡

በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውሮፓ በሚገኙ አባል ሐኪሞች ላይ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት የሆስፒታሉ ግንባታ በሚያልቅበት ጊዜ ከአባሎቻቸው 37 ከመቶ ያህሉ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ለማገልገል እንደሚፈልጉ መረጋገጡን ዶ/ር ተስፋዬ ጠቅሰው፣ የሆስፒታሉ ግንባታ ከሦስት ዓመታት በኋላ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር ሔኖክ ገብረፃድቅ ገብረእግዚአብሔር የልብ ሐኪምና የቡድኑ ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ‹‹በአሁኑ ጊዜ የአባል ሐኪሞቹ ቁጥር ከ200 በላይ ከፍ ማለቱንና ከሐኪሞቹም መካከል ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰሜን አሜሪካ  የቀሩት በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ ሥራ ሲጀምር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያክም ይሆናል ወይ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ሆስፒታሉ ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ዋጋው ከፍ ሊል እንደሚችል፣ በዚህም መሠረት አቅም ለሌላቸው መደገፊያ የሚሆን የኢትዮ-አሜሪካ ሐኪሞች ቡድን ፈንድ መቋቋሙን ዶ/ር ግርማ ተፈራ የቡድኑ የቦርድ ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ፈንድ አማካይነት አቅም የሌላቸውን ለመርዳት ታስቧል፡፡ የሐኪም አባሎቻችን ዋነኛ ፍላጎት ግልጋሎት መስጠት ላይ ያተኮረ ቢሆንም እንደዚህ ያለ ተቋም በበጎ አድራጎት ብቻ ይሥራ ከተባለ ራሱን ሊያኖር አይችልም›› ብለዋል፡፡

አቶ መላኩ ንጉሤ የቡድኑ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰርና ጀነራል ካውንስል የሆስፒታሉ ግንባታ የሚካሄደው በሁለት ምዕራፎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ምዕራፍ  አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚመደብ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለሚያስፈልገው ገንዘብ  ከአባላት ብቻ 20 ከመቶ ያህል መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

የተሰበሰበው ገንዘብ የሕንፃው ዲዛይንና ግንባታውን ለማስጀመር እንደሚያስችልና በተጨማሪም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር በትብብር ለመሥራት መታሰቡን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መወያየታቸውን ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ባንኮች ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

80 የሚደርሱ የኢትዮ አሜሪካን ሐኪሞች ቡድን አባላት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሁለት ቀናት ሥልጠና የሚሰጡ መሆኑም ታውቋል፡፡