የለማ ኦህዴድ ፈተና

 

ጦርነት ታውጆበታል። አስቸኳይ ጊዜ ተደንግጎበታል። ባለስልጣናቱ መናገር አይችሉም። ከተናገሩ ይታሰራሉ። የታሰሩትን የሚከታተላቸው የለም። ዋናዎቹም በትግራይ ደህንነቶችና በሳሞራ ቅልብ ወታደሮች ዓይን ስር ናቸው። መፈናፈኛ ለጊዜው የለም። ድምጻቸው ጠፍቷል። የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት በየመድረኩ ሲያስካኩ ሲፎክሩ፡ የለማ ኦህዴድ ሰዎች ግን ትንፋሻቸው እንኳን የለም። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ድረስ ያለው የለማ ኦህዴድ መዋቅር በትግራይ ደህንነቶች እየተበረበረ አመራሮቹ በኮማንድ ፖስቱ ሰራዊት እየታደኑ ወደ ግዞት እስር ቤቶች እየተወረወሩ ናቸው። የአቶ ለማን የተስፋ መልዕክቶችና ቆራጥ ንግግሮች መከታ ጋሻ አድርገው ለለውጥ የተነሱ ባለሀብቶችም በአባዱላና በአቶ ድንቁ ጠቋሚነት እየተለቀሙ ወደ ማዕከላዊ በመወሰድ ላይ ናቸው።

የትግራዩ ገዡ ቡድን ጥድፊያ ላይ ነው። ጊዜ መስጠት አልፈለገም። እነለማንና አብይን በስብሰባና ግምገማ አፍኖ መዋቅራቸውን በማወላለቁ ዘመቻ ላይ ተጠምዷል። በመካሄድ ላይ ያለውን የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በተመለከተ ከባልደረቦቼ ኤርሚያስ ለገሰና ምናላቸው ስማቸው ጋር በኢሳት እፍታ ፕሮግራም ላይ ውይይት ባደረኩበት ጊዜ የተገለጠልኝ እነ ለማ መታገታቸውን ነው። መግለጫ መስጠት አይችሉም። ክልላቸውን እያስተዳደሩ አይደለም። ካቢኔያቸውን መገናኘትም አይችሉም እየተባለ ነው። ከጨዋታ ውጪ ተደርገዋል። ኤርሚያ ለገሰ መፈንቅለ ድርጅት ተካሂዷል ይላል። ውይይቱን ብታዳምጡ አትከስሩም። በማዳመጥ ለምታጠፉበት ጊዜ የሚቆጫችሁ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ማስፈንጠሪያውን ከዚህ ጽሁፍ ግርጌ አኖርላችኋለሁ።

እናም የእነለማ ኦህዴድ በጅቦች ተከቧል። ከህግ ውጭ፡ አሰራሩ በማይፈቅድ ሁኔታ የትግራዩን ገዢ ቡድን ከሞት ለማዳን በቀቢጸ ተስፋ የተሰለፉት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ነባር አመራሮች ከያሉበት ተለቃቅመው ገብተዋል። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አይደሉም። ምንም ውስጥ ምንም የላቸውም። ነገር ግን ጊዜው ቀውጢ ነው። የሞት ሽረት ትግል የሚካሄድበት ነው። 11ኛው ሰዓት ላይ የሚገኘውን የትግራይ ገዢ ቡድን ህልውና ለማትረፍ መረባረብ አለባቸው። የሚቧጠውን ቧጠው፡ የሚነከሰውንም ነክሰው ማፊያ ድርጅታቸውን ለማዳን ከስብሰባ አዳራሽ ገብተዋል። ይሉኝታን ከነመፈጠሩም የማያውቁት፡ ህሊናቸውን ገና ተከዜን ተሻግረው ሲዘልቁ በእንዶድ አጥበው የተገላገሉት፡ ከዕውቀትም፡ ከዕውነትም የተጣሉት፡ የዘመኑ ጎልያዶች፡ ተጠራርተው ተሰይመዋል። የመጨረሻ ሙከራ ነው። ይህ ስብሰባ ሁሉ ነገር ይለይለታል። ጀጋኑ፡ ተጋዳላይ፡ ወዲዎች!

እርጅናና የአልኮል ሱስ የተንኮልና ሴራ አቅሙን ያላዳከመው ስብሃት ነጋ ያጉረጠርጣል። የማይድን በሽታ የሚያሰቃየውና በመድሃኒት ጉልበት ቆሞ የሚሄደው ስዩም መስፍን ለዚህ ስብሰባ የሚሆን አቅም አላጣም። ቴድሮስ ሀጎስ ከመቀሌ ገብቷል። አለቃ ጸጋዬ በርሄ ከቴልሃቪቭ በሮ መጥቷል። የስብሃት ነጋ ምርኩዝ ጠባቂ የሚባለው አባዲ ዘሙም አልቀረም። የሙስናው ባላባት ወዲ አባይ ጸሃዬ ፊት ወንበር ላይ ጉብ ብሏል። እነዚህ ስድስት የትግራይ ገዢ ቡድን ነባር አመራሮች በህውሀትም ሆነ በኢህ አዴግ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ የሉም። ግን ተሰይመዋል። በወሳኙ ስብሰባ ላይ ወንበር ይዘው ተቀምጠዋል። ኤርሚያስ እነዚህን ሰዎች በዱር እንስሳ መስሏቸዋል። የትግራይ የበላይነት ላይ አደጋ የደቀኑትን ሰልቅጠው ለመብላት የተሰለፉ አውሬዎች።

ስብሰባው ሀገ ወጥ ነው። የእነዚህ ሰዎች መገኘት ብቻውን ጨዋታውን ያፈርሰዋል። ሳይጀመር ውጤቱ የታወቀ ስብሰባ ላይ እነለማ ምን ይሰራሉ? ምን ይጠብቃሉ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእርግጥ ጥያቄው ተገቢ ነው። እነዚህ የትግራይ ቡድን ነባር አመራሮች የተገኙት ለምን እንደሆነ ይታወቃል። ከየብሄራዊ ድርጅቶቹ ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ስብሰባ ላይ ያለስልጣናቸው፡ ያለወንበራቸው ወንበር ይዘው የተቀመጡት እነስብሃት ምን እያሸተቱ እንዳለ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ለማጣፈጫነት ከሌላውም ድርጅት ነባር የሚባሉ አመራሮች መግባታቸው አልቀረም። እንደነካሱ ኢላላ ዓይነት ህወሀትን በጉርምስናው ዘመኑ የተጠመቀ የደኢህዴን አመራርም በስብሰባው ላይ ተገኝቷል። ዓላማው የእነስብሃትን መገኘት ምክንያታዊ ለማድረግ ነው። ደግሞም ካሱ ኢላላ ከስብሃት በላይ ህወሀት መሆኑን ለሚያውቁ የቅርብ ሰዎች ጉዳዩ በሚገባ ግልጽ ይሆንላቸዋል።

እንግዲህ እነስብሃት ተሰባስበው የገቡበት ስብሰባ በዝግ እየተካሄደ ነው። የትግራይ ገዢ ቡድንን ህልውና በማይናወጥ መሰረት ላይ ተክሎ ዳግም የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦና ጨፍልቆ ለመግዛት የሚያስችል አቋም ላይ ለመድረስ እንደሆነ አያያዙ ይመሰክራል። ከአዳራሹ ውስጥ እነስብሃት የለማን ቡድን ወጥረው ይዘዋል። ከአዳራሽ ውጪ ኮማንድ ፖስቱ የለማን መዋቅር እየመታ ነው። እነለማ ከውስጥም ከውጭም እየተጠቁ ናቸው። የትግራይ ገዢ ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የፈለገበት ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍንትው ብሎ የታየበት ሆኗል። በረከት ስምዖንን ጨምሮ መላው የደኢህዴን አመራር እነለማ ላይ የጭቃ ጅራፍ እየሰነዘረ እንደሆነም ይሰማል። እነስብሃት ሂሳብ ሰርተው የገቡበትን ትወና በረከት፡ ካሱና ሌሎች በሚገባ እየተጫወቱት ነው።

የአጋች ታጋች ድራማው ቀጥሏል። እነለማ በአውሬዎች ተከበዋል። ጥያቄው በዚህ ሁኔታ እነለማ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚል መሆን አለበት። ምን ምርጫ አላቸው? ከካቢኔው የተቆራረጠ፡ አፉ የተሸበበ፡ መተንፈስ ብቻ የተፈቀደለት የለማ አመራር በዚህ ወቅት ላይ ተስፋው ማን ነው? በእርግጥ ከስብሰባው አዳራሽ ምን እየተካሄደ እንዳለ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ሽፈራው ሽጉጤ የሚባል ሰው ብቅ ጥልቅ እያለ ከሚወረውራት ቁራጭ መረጃ በቀር ሌላ ነገር የለም። ጭምጭምታዎች የሚያመላክቱት እነለማ በተከላካይነት መስመር ላይ መሆናቸውን ነው። አቅም እያጡ የመጡ ይመስላል። ጓዶቻቸውን ከጅቦች መንጋ ማስጣል ያልቻሉት እነለማ የታዬ ደንደአ፡ የአምስት ከፍተኛ የኦህዴድ አመራሮች እስር ላይ ዝምታቸው የሚነግረን ያሉበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ መሆኑን ነው።

በእርግጥ እነለማ በመጨረሻ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው። ሁለት ምርጫዎች ግን አላቸው። አንደኛው የአውሬዎቹን የሚያፏጭ ጥርስ አንበርክኳቸው፡ እጅ ሰጥተው ኦህዴድን ወደ ቀድሞው የአሽከርነት ዘመኑ በመመለስ በአሳፋሪ የታሪክ ገጽ ላይ ስማቸው ትተው ማለፍ ነው። ሁለተኛው ምርጫ የአወሬዎቹን ጥርስ ለማራገፍ ቆርጦ የተነሳውን ህዝባቸውን ተስፋ አድርገው መፈንቅለ ስብሰባ ከተካሄደበት አዳራሽ ውልቅ ብሎ መውጣት ነው። ሁለቱም ምርጫዎች ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም። የመጀመሪያው ምርጫ ለእነለማ የቁም ሞት ነው። የእነስብሃትን የተሳለ ቢላዋ በመፍራት በተዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ ዘው ብሎ መግባትን ምርጫቸው ካደረጉ የእነለማ ታሪክ በክህደት መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲወቀሱ ይኖራሉ። እየሰጠመ ካለው መርከብ ጋር አብረው ሰጥመው ከትውልድ ትውልድ እየተረገሙ ይነሳሉ።

ምርጫቸው ሁለተኛው ከሆነ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ሲወደሱ ይኖራሉ። ህዝባቸው ተነስቷል። የትግራዩን ገዢ ቡድን እያንቆራጠጠ ነው። በማያቋርጥ ህዝባዊ ማዕበል እያላጋው ነው። ይህ የህዝብ ሃይል እነዚህን የዘመኑ ጉግማንጉጎችን ጠራርጎ የታሪክ ቆሻሻ በምድረግ ሊቀብራቸው ከጫፍ ደርሷል። እነለማ ሁለተኛውን ምርጫ ከተከተሉ የሚከፍሉት ጊዜያዊ ዋጋ ነው። ምናልባትም እስር። ይሄው ጓዶቻቸው እየታሰሩም አይደል?! እነታዬ ደንደአ የታሰሩት ሰርቀው አይደለም። ነፍስ አጥፍተው አይደለም። ለቆሙለት መርህና የህዝብ ወገኝተኝነት እስከመጨረሻው ቃላቸውን በመጠበቃቸው ነው። ታዲያ እነለማ ምን ያስፈራቸዋል? እነታዬ እየከፈሉ ካሉት መስዋዕትነት በላይ ምን ዋጋ ሊከፍሉ እጅ ይሰጣሉ?

ይህ ሳምንት የለማ ኦህዴድ ቁርጡ ይለይለታል!!!!!

Advertisements

የኢትዮጵያው ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማጽደቁን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አወገዘ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 23/2010) የኢትዮጵያው ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማጽደቁን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አወገዘ። አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ፓርላማው የሕዝቡን ድምጽ ከመስማት ይልቅ አፈናን ለማራመድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማጽደቁ እጅግ የሚያበሳጭና ሃላፊነት የጎደለው ነው። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሐፊ ሳሊል ሸቲ የኢትዮጵያ ፓርላማ በዚህ አስቸጋሪና የፖለቲካ ቀውስ በተፈጠረበት ሁኔታ የሕዝቡን ድምጽ ሊሰማ ይገባ ነበር ብለዋል። አሁን የሚያስፈልገው የሕዝቡን ሰብአዊ መብት ማክበር እንጂ አፈና የሚያመጣው መፍትሄ የለምም ነው ያሉት። እንደ ዋና ጸሃፊው ሳሊል ሻቲ ገለጻ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ተደንግገው በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ተፈጽመዋል። እነዚህም ግድያዎች ጅምላ እስሮችና በሃይል መፈናቀልን እንደሚጨምርም ነው የገለጹት። እናም አሁን ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማጽደቅ ተመሳሳይ ሕገወጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት የሌላቸውን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እንዲፈጸሙ መስማማት ነው ባይ ናቸው። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊዋ ፓርላማው የሕዝቡን ድምጽ ከመስማት ይልቅ አፈናን መምረጡ እጅግ የሚያበሳጭና ሃላፊነት የጎደለው ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት አዋጁን እንዳያጸድቁ በሕዝብም ሆነ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በኩል ቢጠየቁም በጉዳዩ ላይ 88ቱ አባላት ቢቃወሙም 346ቱ የድጋፍ ድምጽ ሰጥተዋል። ይህ ቁጥር ግን ከፓርላማው ጠቅላላ አባላት 2/3ኛ ድምጽ እንዳልሆነ ይታወቃል። ስለሆነም ፓርላማው ቁጥሩን አስተካክሎ የ395 ድምጽ ድጋፍ ተገኝቷል ማለቱ ሁኔታውን አወዛጋቢ አድርጎታል።

amnesty-international-logo-1

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ መደበኛ ስብሰባውን በአሻፍንበርግ ከተማ አካሄደ

News Report by Alemayehu kidanewold

Photo by Michael Mekonnen

በየሶስት ወሩ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ መደበኛ ስብሰባውን February 10,2018 በአሻፍንበርግ ከተማ አካሄድዋል:: በስብሰባው ላይም ብዛት ያላቸው የድርጅቱ አባላት የተገኙ ሲሆን ወቅታዊ ሰለሆነውም የሃገራችን ሁኔታ በሰፊው ተወያይተዋል::

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ መደበኛ ስብሰባውን በድርጅቱ ዋና ሊቀመንበር በአቶ ልዑል ቀስቅስ የመክፈቻ ንግግርና የሃገራችን የወቅቱን የፖተቲካ ሁኔት በማንሳት የተጀመረውን ትግልና የህዝብ እንቢተኝነትን በመደገፍ ምንጊዜም ከጎኑ ልንቆምለት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል::

የወያኔ ስርአት ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የራሱን የስልጣን እድሜ ለማራዘም የሚያደርገውን ያለፈበትን ብልጠት በቃህ ልንለውና ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄርን ከብሄር ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩትን ሰዎች ለይቶ በማወቅ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለአንድ አላማ በጋራ መቆም እንደሚገባውም አሳስበዋል::

ተሳታፊዎቹም አሁን የደረስንበት የለውጥ ሰአት በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን ብዙዎች የተሰዉበትና ብዙዎችም ለእስር ፣ ለእንግልትና ለስደት ያበቃ በመሆኑ በምንም ተአምር ተመልሶ እንዳይገለበጥ እና ተመልሰን ወደ ድሮው ሰቃይና መከራ ላለመግባት ሁሉም ለውጥ ፣ ሰላምና ዲሞክራሲ ወዳድ ኢትዮጵያዊን በአንድነት ሊቆምና በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም ወገኖች ጋር ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲጀምር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010) የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም ወገኖች ጋር ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲጀምር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ። የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በድንገት ከስልጣን የመልቀቅ ርምጃም በሃገሪቱ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን መደቀኑን ህብረቱ አስታወቋል። የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ባሰራጨው በዚህ መግለጫ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደገና መታወጁም በዘላቂ መፍትሄ ጥረቱ ላይ አደጋ መደቀኑንም ገልጿል። በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚዋቀረው መንግስት የተጀመሩ በጎ ርምጃዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሙሉ አቅም ሊኖረው እንደሚገባም አሳስቧል። ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር የሚደረግ ንግግር ለቀውሱ ዘላቂና ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚያመጣ የገለጸው የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት፣ተቃዋሚዎች፣መገናኛ ብዙሃንና ሲቪል ሶሳይቲ መካከል ንግግር እንዲጀመርም ጥሪ አቅርቧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደገና ተመልሶ መምጣቱ ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋውን ለአደጋ ማጋለጡን ሆኖም በአጭር ጊዜ ገደብ ውስጥ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥሪ ቀርቧል። በሃገሪቱ ሕገ መንግስት የሰፈሩ ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም መሰረታዊ ነጻነቶች እንደተጠበቁና የአመጽ ድርጊቶችም እንዲወግዱ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይና ሴኪዩሪቲ ፖሊሲ ቃል አቀባይዋ ካትሪን ሬይ በኩል ባወጣው መገለጫ አሳስቧል።

flag

የእነ በቀለ ገርባ ክስ ተቋረጠ

የእነ በቀለ ገርባ ክስ የተቋረጠው… በእነ ጃዋር የአመጽ ጥሪ ወይስ በመንግሥት ዕቅድ? እነ ኦቦ ለማ የእነ ኦቦ በቀለ ገርባን ክስ አስቋረጡ ወይስ የፌዴራል መንግሥት አመጹን ተከትሎ ወሰነው?
(የኦሮሞ ሕዝብ፣ የእነ ጃዋር እና የእነ ለማ ፖለቲካዊ አጨዋወት አንድ አቅጣጫን የያዘ ይመስላል። የሚፈልጉት ሁሉ እየሆነ ነውና።)

የሀገራሽን ጉምቱ ጉምቱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከጠባቡ ወህኒ ቤት እየወጡ ነው። እንኳን በጠባቡ ከመታሰር በሰፊው ወደ መታፈን መጥታችሁ ተቀላቀላችሁን ብለናል።

ብአዴን ስብሰባ ላይ ነው። ብአዴን አማራን እወክላለሁ የሚል ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች አባላት ያሉት ድርጅት ነው። (ቆይ ግን ከዚህ ላይ ብአዴንን ምን አስነሳኝ? 🙂 ) “ብአዴን ቢሰበሰብ ባይሰበሰብ… ቢመክር ባይመክር… ምን ይጠቅማል? ምንስ ለውጥ ያመጣል?” ብሎ ለማቃለል ይከብዳል። ማን ያውቃል… ብአዴንም ተለውጦ የምር የአማራ ሕዝብ ትምክህት ይሆን ይሆናል። ኦህዴድን በዚህ ደረጃ የኦሮም ሕዝብ ልብና ሳንባ ይሆናል ብሎ ማን ገምቶ ነበር??? እና ከብአዴንስ በጎውን ብንመኝ ማን ከልክሎን? አንዳንዴ… በፖለቲካ ዓለም ጠላቴ ያልኸው ነፃ አውጭ ወዳጅህ የመሆን ዕድሉ ዝግ አይደለም።

ለማንኛውም… የሀገሬ ፖለቲካ… ያው የአፍሪካ ፖለቲካ ነው። ከግጭትና ከደም ለመጽዳት ገና ብዙ ዘመናትንና ትውልድን ይጨርሳል።

27749995_1643343012425444_1284994562179587141_n

“ጠበቆች ከተነሱ ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም” ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን

 

Oromo Federalist Congress leaders.

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት የድርጅቱ አመራሮች በድጋሜ በችሎት መድፈር ተፈረደባቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖ ክስ መዝገብ የተከሰሱትን ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ እና በቀለ ገርባ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባለመነሳታቸው ችሎቱን ደፍረዋል በሚል በአራቱም ላይ የ6 ወር የእስር ቅጣት አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ካልተነሱ ማንነታቸውን መለየት እንደማይቻል በመግለፅ ጠበቆቻቸው መክረው እንዲያስነሷቸው ጠይቋል።

ሆኖም ተከሳሾቹ “ባለፈው በመናገራችን ተቀጥተናል” በሚል አንነሳም ማለታቸውን በጠበቆች በኩል ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ተከሳሾቹ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባይነሱም እጃቸውን ያወጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ካልተነሱ የፍርድ ቤቱን ሕግ ስላላከበሩ እርምጃ እንወስዳለን ብሏል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን በበኩላቸው በፍርድ ቤት ማንነትን ማረጋገጥ የሚያስፈልገው ክስ ሲነበብ እንደሆነ፣ መዝገቡ ለዛሬ ጥር 28/2010 የተቀጠረው ለክስ መስማት (ማንበብ) ሳይሆን ፍርድ ለመስጠት ስለሆነ ጠበቆቹ ከቆሙ ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም ብለዋል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባለመቆማቸው ምክንያት የፍርድ ቤቱ ሰዓት በ30 ደቂቃ እንደባከኑና ድርጊቱንም ችሎት መድፈር መሆኑን በመግለፅ ውሳኔውን አስተላልፏል። ተከሳሾቹ ጥር 10/2010 በነበረው ቀጠሮውም በችሎት መድፈር በ6 ወር እስር መቀጣታቸውን አስታውሶ፣ ከባለፈው አልተማሩም በሚል ለ2ኛ ጊዜ የ6 ወር እስር ቅጣት ወስኗል። ጥር 10/2010 ዓም ችሎት ደፍራችኋል በተባሉበት ወቅት በፍርድ ቤት የተናገሩት ተከሳሾቹ ስለዛሬው ውሳኔው አልተናገሩም።

በሌላ በኩል 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ፣ 12ኛ ተከሳሽ ተስፋየ ሊበንና 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ በቀጠሮው መሰረት ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ዛሬ በችሎት መድፈር 6 ወር የተፈረደባቸውን አራቱን አመራሮች ጨምሮ በሁሉም ላይ ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 28/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።

ሰላም ባስና ዳሽን ቢራ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው

(ኢሳት ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተጠራ አድማና ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰላም ባስና ዳሽን ቢራ አስታወቁ።

የቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ያነጋገራቸው የሁለቱ ድርጅቶች ሃላፊዎች እንዳሉት በአድማውና በጥቃቱ ምክንያት ከኪሳራ ባሻገር ህዝቡ በአገልግሎታችን እንዳይጠቀም ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥሯል።

ሰላም ባስ በአራት መስመሮች አገልግሎት ማቋረጡን ሲያሳውቅ ዳሽን ቢራ በተለይ በባህርዳር ከፍተኛ የተቀባይነት ቀውስ እንደገጠመው ገልጿል።

ለቢቢሲ አማርኛ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የሰላም ባስ አገልግሎት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሀጎስ አባይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ህዝቡ በሰላም ባስ ለመጠቀም ፍራቻ አድሮበታል።

በዚህም ምክንያት የገቢ መቀነስ ታይቷል ሲሉ ገልጸዋል።

በቅርቡ ወደቁልቢ ገብርዔል በመጓዝ ላይ በነበሩ አራት የሰላም ባስ አውቶብሶች ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ መስታወቶቻቸው መሰባበሩን አቶ ሀጎስ አስታውሰዋል።

ሁለት የሰላም ባሶች በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች መቃጠላቸውንም ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።

ሰላም ባስ በመላ ሀገሪቱ በ17 መስመሮች አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ሀጎስ በተፈጠረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት የአራቱ መስመሮች አገልግሎት መቋረጡን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በሀረር፣ ድሬዳዋ፣ ጂጂጋና አሶሳ መስመሮች ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ መቋረጡን ለማወቅ ተችሏል።

በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግር አልገጠመንም ብለው መናገር ያልደፈሩት አቶ ሀጎስ አባይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አልደረሰብንም በሚል አልፈውታል።

በጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ጊዜ በርካታ የሰላም ባስ አውቶብሶች ጥቃት የተሰነዘረባቸው መሆኑ ይታወሳል።

በቅርቡም በወሎ ኡርጌሳና በሰሜን ሸዋ አጣዬ መስመር ተመሳሳይ ጥቃትና እገታ በሰላም ባስ ላይ መደረጉን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

ስራ አስኪያጁ አቶ ሀጎስ አባይ በገቢ ደረጃም ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በዘንድሮ ገቢያችን መቀነሱን አውቀናል ብለዋል።

ሰላም ባስ ከኢትዮጵያ ህዝብ በተዘረፈ ገንዘብ የተቋቋመው የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርት ንብረት በመሆኑ በመላ ሀገሪቱ አድማ እንደተጠራበት ይነገራል።

አቶ ሀጎስ ግን ያስተባብላሉ። በአክሲዮን የሚተዳደር ድርጅት ነው በማለት።

በሌላ በኩል በባህርዳር ከተማ በአንድ ቀን ከ60 በላይ ዜጎች በአጋዚ ሰራዊት መገደላቸውን ተከትሎ አድማ የተጠራበት ዳሽን ቢራም ተመሳሳይ ቀውስ እንደገጠመው እየተነገረ ነው።

የፋብሪካው ምክትል ስራአስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ማሩ ለቢቢሲ አማርኛ እንደተናገሩት ዳሽን ቢራ በተለይ በባህርዳር ከፍተኛ ተጽዕኖ ተፈጥሮበታል።

ኪሳራ ባይገጥመንም ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ትርፋችን ቀንሷል ብለዋል አቶ ሙሉጌታ።

ለጥይት መግዣ ገንዘብ አንሰጥም በሚል አገልግሎታችን ላይ አድማ መመታቱ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ ሙሉጌታ እንደሌሎች ድርጅቶች ለመንግስት የምንክፍለው ግብር ብቻ ነው ሲሉም አስተባብለዋል።

በአማራ ክልል ዳሽን ቢራ የሚያዘጋጃቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች በተደጋጋሚ አድማ ተመቶባቸው የተቋረጡ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ቢቢሲ አማርኛ ያነጋገራቸው አንድ የባህርዳር ነዋሪ እንዳሉት በባህርዳር ዳሽን ቢራ መጠጣት አደጋ አለው።