Tag Archive | እንደዘበት ወጥቶ መቅረት

እንደዘበት ወጥቶ መቅረት

ሳሙኤል አወቀን ይበልጥ የማውቀው በተለይ በመጣጥፎቹ ነበር፡፡ ለካ ነበር እንደዚህ ቅርብ ነው ነበር ያሉት እቴጌ ጣይቱ? ገና በግንባር ሳንተዋወቅ በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ተወቃቅሰንም ነበር፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት በመጣበት ወቅት እምላዕሉ ማለት አንተ ነህ ብሎኝ ስንተዋወቅ በጣም ፈጣን እና በተፈጥሮው በሳል ልጅ መሆኑን ለመረዳት ትንሽ ደቂቃ እንኳን አልፈጀብኝም ነበር፡፡ ቅምም ያለ ቀልጣፋ ልጅ ዳግም ላናየው እንደፅጌረዳ በሰው እጅ ተቀጠፈ፡፡ ከአሰፋ ማሩ ጎን በአርያም ሆኖ ሊፋረደን ከአለት የጠጠረ አደራውን ትቶልን እንደወጣ ቀረ፡፡ እነሆ ሃገር እንደ ድመት ልጆቿን እንደምትበላ የምናስመሰከርበት አርባኛ አመታችንን ሳሙኤልን እንደሻማ ለኩሰን አከበርንላት፡፡ ሰው እንዴት ወገኑን፣ያገሩን ልጅ፣ ያውም ወደፊት ለትውልድ አርአያ ሊሆን የሚችል ጎረምሳ በአጭር ሲያስቀር ህሊናው እረፍት ይሰጠዋል? ምን የሚሉት እርግማን እና ልክፍት ተጣብቶን ይሆን አርባ አመት ሙሉ እንደጅብ እርስ በርስ እየተበላላን እንደማሽላ ፍሬ ብቅ ብቅ ያለውን ከነተስፋው የምንቀጨው? የምን ሾተላይ ይሆን? በምድር ጽዋችን ሞልቶ ሲቃችንን የሚያይ እምባችንን የሚያብስ በደላችንን የሚሰማ አምላክ እውነት ከወዴት ይሆን የሚኖረው? ለምንስ ይሆን ዝም ያለን??????????
እህህ…….
ምርር ስቅስቅ ብዬ አላነባው ነገር፣
ሲቃም አመጽ ተብሎ እንዳልጠረጠር፣
እምባዬን እንደህል ሲያንቀኝ እየዋጥኩት፣
ለቆሰለው አንጀቴ ቀለብ አደረኩት፡፡

እምላዕሉ ፍስሃ

1505152_1428343147489663_4996375091015041984_n